የዓለም ካቶሊካውያን አባት በአፍሪካ ሊያደርጉት የነበረውን ጉብኝት ማራዘማቸው እያነጋገረ ነው
አባ ፍራንቼስኮስ ከርዕሳነ ሊቀ ጳጳስነት ሊለቁ እንደሚችሉም ነው እየተነገረ የሚገኘው
አባ ፍራንቼስኮስ የካናዳ ጉዞ እቅዳቸውን አለማራዘማቸው ተነግሯል
የዓለም ካቶሊካውያን አባት አባ ፍራንቼስኮስ በአፍሪካ ሊያደርጉት የነበረውን ጉብኝት ማራዘማቸው እያነጋገረ ነው።
የ85 ዓመቱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቼስኮስ ባሳለፍነው ሳምንት በደቡብ ሱዳን፤ በመጪው ወርሃ ሐምሌ ደግሞ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንኮ ሊያደርጉት የነበረውን ጉብኝት አራዝመዋል።
ፍራንቼስኮስ ካጋጠማቸው የእግር ህመም ጋር በተያያዘ ጉብኝቱን ማራዘማቸው ነው የተነገረው።
ህመሙ በቅርቡ በዊልቸር ጭምር እንዲንቀሳቀሱ አስገድዷቸው ነበር።
ሆኖም በመጪው ነሐሴ ካናዳን ለመጎብኘት የያዙት ዕቅድ አለመራዘሙ ተነግሯል።
ይህም የአፍሪካውን ጉዞ መራዘም በቅርቡ እንደሚካሄድ ከሚጠበቀው የካርዲናሎች ጉባኤ ጋር ያያያዙ ብዙዎች ፍራንቼስኮስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስነቱን በፈቃዳቸው ሊለቁ እንደሚችሉ ያመላከተ ነው ሲሉ ገልጸውታል።
በነሐሴ ወር እንደሚደረግ በሚጠበቀው ጉባኤ የሚሰየሙ አዳዲስ ካርዲናሎች ሊኖሩ ይችላሉ መባሉ አባ ፍንቼስኮስም ሊተኩ ይችላሉ የሚል ጥርጣሬን አስነስቷል።
ሆኖም ለቫቲካን ጉዳዮች ቅርበት ያላቸው ብዙዎች ፍንቼስኮስ ይለቃሉ ብለው አያስቡም።
ኤ.ኤፍ.ፒ አናገርኳቸው እንዳላቸው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ከሆነ ጉዳዩ አዛውንቱ በሌላ እንዲተኩ ፍላጎት ባላቸው አካላት የሚነዛ አሉባልታ ነው።