የአውሮፓ ህብረት፤ ሀገራት በኮፕ-27 ስብሰባ ባሳዩት የቁርጠኝነት ማነስ “ቅር መሰኘቱን" ገለጸ
የበለጸጉ ሀገራት እያደጉ ላሉ ሀገራት የ100 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ቢገቡም ቃለቸውን አላከበሩም
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ምክትል ፕሬዝዳንት “የሞራል ችግር ገጥሞናል” ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል
የአውሮፓ ህብረት በግብጽ በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት ኮፕ-27 የመሪዎች ጉባኤ ላይ በተደረሰው የአየር ንብረት ስምምነት ላይ ያለውን የልቀት መጠን ለመቀነስ ፍላጎት በማጣቱ ብስጭቱን ገልጿል።
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ፍራንሲስ ቲመርማንስ በቀይ ባህር በሻርም ኤል ሼክ ሪዞርት በተካሄደው የመሪዎች ጉባኤ የመዝጊያ ስብሰባ ላይ "የአውሮፓ ህብረት እዚህ የመጣነው ጠንካር ባለ ቋንቋ ለመስማማት ነበር ይህንንም አለማድረጋችን ቅር ብሎናል" ሲሉ መናገራቸው ኤኤፍፒ ዘግቧል።
በግብጽ በሻርም ኤል ሼክ ከተማ ሲካሄድ የቆየው 27ኛው የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በዛሬው እለት ተጠናቋል፡፡
ቲመርማንስ የአየር ንብረት ተጽዕኖ ተጋላጭ የሆኑ ሀገራትን ለማካካስ በ ኮፕ-27 ላይ “ኪሳራ እና ጉዳት” ፈንድ መፈጠሩን ለመደገፍ የአውሮፓ ህብረት መወሰኑንም ጠቁመዋል፡፡
ህብረቱ ቀደም ሲል ተጠያቂነትን ሊያስከትል ይችላል በሚል ስጋት በጉበኤው ለተነሳው ሃሳብም ተቃውሞውን ገልጿል።
ቲመርማንስ በጉባኤው የተነሱትን ከሃላፊነትን የመሸሸ የሚመስሉ ሃሳቦች በመንተራስ ሲናገሩም “የሞራል ችግር ገጥሞናል፣ ምክንያቱም ይህ ስምምነት የገጠመንን ከባድ ፈተና ለማቃለል በቂ አይደለም” ብለዋል።
ፈረንጆቹ 2015 በፈረንሳይ በተካሄደውና የፓሪስ ስምምነት ተብሎ የሚታወቀው 21ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ የዓለም ሀገራት አንድ ላይ ተባብረው ከሰሩ የሙቀት መጠኑ ከ1 ነጥብ 5 ሴልሺዬስ በላይ እንዳይሆን ማድረግ እንሚቻል የሚያትት ስምምነት መፈረማቸው አይዘነጋም።
ያም ሆኖ ሀገራቱ ስምምነቱን ተግባራዊ ከመድረግ አኳያ ከፍተኛ የሆነ ክፍተት እንዳለ ሀገራቱ የአሁኑን ጫምሮ ከዛ በኋላ ባደረጓቸው ሰባት ጉባኤዎች ሲያነሱ ይደመጣል።
በፓሪሱ ጉባኤ የበለጸጉ ሀገራት እያደጉ ላሉ ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን እንዲቋቋሙ የ100 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ቢገቡም በቃላቸው ሊገኙ አልተገኙም።
ይህም በምግብ ራሷን ለማቻል ጥረት በማድረግ ላይ ላለችው አፍሪካ “የአየር ንብረት ለውጥ” ከባድ ፈተና እንደሆነባት ይነገራል።
እናም በግብጽ ሲካሄድ የሰነበተውና በዛሬው እለት ህዳር 20 ቀን 2022 የተጠናቀቀው የ“ሻርም ኤል-ሼክ ጉባኤ (ኮፕ-27)” ብዙም አጥጋቢ ውጤት የማይገኝበት ከሆነ አደጋው ከዚህም የከፋ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡
ከግማሽ በላይ የሚሆነው የዓለም የግሪን ሃውስ ጋዝ የሚለቀቀው ከአሜሪካ፣ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ህንድ እና ጀርመን እንደሆነ ይታወቃል።