የዓለማችን አሳሰቢ ጉዳይ ስለሆነው አየር ንብረት ለውጥ ምን ያውቃሉ…?
የግሪን ሃውስ ጋዝ ልቀቶችና ሚቴን ለዓለም የሙቀት መጨመር ከ90 በመቶ በላይ አስተዋጽዖ ያበርክታሉ ተብሏል
ተመራማሪዎች የአየር ንብርት ለውጥ ላይ እርምጃ ካልተወሰደ በያዝነው ክፍለ ዘመን ብቻ እስከ 550 ዝርያዎች ይጠፋሉ ባይ ናቸው
በሰው ልጅ ድርጊት ምክንያት የምድራችን ሙቀት መጠን ከቀን ቀን እየጨመረ የመምጣቱ ነገር አሁንም ኣሳሳቢ ጉዳይ ሆኖ እንደቀጠለ ነው።
አሁን ላይ በዓለማችን እየጨመረ ባለው የሙቀት መጠን ምክንያት አንዳንድ ስፍራዎች ወደ በረሃነት እየተቀየሩ መሆናቸው በሌላ በኩል ደግሞ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት አንዳንድ የዓለማችን ክፍሎች ባጋጠማቸው ከፍተኛ የዝናብ መጠን ምክንያት ለጎርፍ ሲጋለጡ ማየት የተለመደ ሆነዋል።
በየቦታው እየታየ ያለው ድርቅ፣ የውቅያኖሶች መጠን መጨመር፣ ሰደድ እሳት እንዲሁም የበርካታ ነብሳት ከምድራችን መጥፋት የአየር ንብረት ለውጡ ከፊታችን ያለው ፈተና እጅጉን እንሚያከብደው ለመገመት አያዳግትም።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ፤ ዓለማችን በ19ኛው ክፍለ ዘመን ከነበረችበት የሙቀት መጠን አሁን በ1 ነጥብ 2 ዲግሪ ሴልሺዬስ ገዳማ ጨምራለች። ወደ አየር ንብረት የሚለቀቀው የካርበን ዳይኦክሳይድ መጠንም በ50 በመቶ ጨምሯል።
በከባቢ አየር ውስጥ ያለው የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠንም በ3 ሚሊዮን ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል።
ለዚህም የግሪን ሃውስ ጋዝ ልቀቶች እና ሚቴን ለዓለም የሙቀት መጨመር ከ90 በመቶ በላይ አስተዋጽዖ እንደሚያበረክቱ ጥናቶች ያመለክታሉ።
የዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት ፤ የአየር ንብረት ለውጥን በ21 ኛው ክፍለ ዘመን ለዓለም ጤና ትልቅ ስጋት ነው ሲል መግለጹ የታወቃል።
የዘርፉ ተመራማሪዎች፤ የአየር ንብረት ለውጥ ይዞት የሚመጣውን መዘዝ ለማስቀረት ዋነኛ መፍተሄው የሙቀት መጠንን መቀነስ እንደሆነ ይናገራሉ።
ይህም የምድራችን የሙቀት መጠን “በ1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴልሺዬስ መገደብ” እንደማለት መሆኑ ይገልጻሉ።
ርምጃ መውሰድ ካልተቻለ የምድራችን ሙቀት መጠን በያዝነው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ወደ 2 ድግሪ ሴልሺዬስ ከፍ ሊል እንደሚችል የሚያስጠነቅቁት ተመራማራዎቹ፤ የሙቀት መጠኑ ከጨመረ በሰው ልጆችም ሆነ በእንስሳት ላይ አስከፊ የሚባሉ ነገሮች የመከሰት እድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ ያሳስባሉ።
በተለይም ምጣኔ ኃብታቸው ያላደገ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ከመቸገራቸው የተነሳ ለከፍተኛ ችግር እየተዳረጉ ነው።
በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት፣ ፓኪስታን ፣ አፍጋኒስታን፣ ሶሪያ፣ የመን እና በሌሎች ሀገራት እየታየ ያለው ድረቅና የመግብ እጥረት ለዚሁ ሁነኛ ማሳያ እንደሆነም ነው የተመድ መረጃዎች የሚያሳዩት።
ዓለማችን ሞቃታማ እየሆነች በመጣች ቁጥር ከሰው ልጅ ባሻገር እንስሳት ምግብ ፈልጎ መብላትና ውሃ መጠጣት እየከበዳቸው እንደሚመጣም የሚታወቅ ነው፡፡
ተመራማሪዎች ችግሩን ለመግታት እርምጃ ካልተወሰደ በያዝነው ክፍለ ዘመን ብቻ እስከ 550 ዝርያዎች ሊጠፉ ይችላሉ ባይ ናቸው።
ዓለም ምን እየሰራ ነው…?
በፈረንጆቹ 2015 በፈረንሳይ በተካሄደውና የፓሪስ ስምምነት ተብሎ የሚታወቀው 21ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ የዓለም ሀገራት አንድ ላይ ተባብረው ከሰሩ የሙቀት መጠኑ ከ1 ነጥብ 5 ሴልሺዬስ በላይ እንዳይሆን ማድረግ እንሚቻል የሚያትት ስምምነት መፈረማቸው አይዘነጋም።
ያም ሆኖ ሀገራቱ ስምምነቱን ተግባራዊ ከመድረግ አኳያ ከፍተኛ የሆነ ክፍተት እንዳለ ሀገራቱ ከዛ በኋላ ባደረጓቸው ስድስት ጉባኤዎች ሲያነሱ ይደመጣል።
በፓሪሱ ጉባኤ የበለጸጉ ሀገራት እያደጉ ላሉ ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን እንዲቋቋሙ የ100 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ቢገቡም በቃላቸው ሊገኙ አልተገኙም።
ይህም በምግብ ራሷን ለማቻል ጥረት በማድረግ ላይ ላለችው አፍሪካ “የአየር ንብረት ለውጥ” ከባድ ፈተና እንደሆነባት ይነገራል።
እናም በዛሬው እለት ህዳር 6 ቀን 2022 በግብጽ የተጀመረው የ“ሻርም ኤል-ሼክ ጉባኤ (ኮፕ-27)” የዓለም ሀገራት በተለያዩ የአየር ንብረት አንኳር ጉዳዮች ላይ በመምከር ተግባራዊ ምላሽ የሚሰጡበት እንደሚሆን ይጠበቃል።
በተጨማሪም ጉባኤው የአየር ንብረት ለውጥ በ2023 በአፍሪካ ላይ የሚፈጥረውን ተጽዕኖ በተመለከተ በቂ ግንዛቤ የሚያዝበት እንደሚሆን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከግማሽ በላይ የሚሆነው የዓለም የግሪን ሃውስ ጋዝ የሚለቀቀው ከአሜሪካ፣ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ህንድ እና ጀርመን እንደሆነ ይታወቃል።