የአውሮፓ ህብረት የ70 ቢሊዮን ዩሮ ጦር መሳሪያ ግዢ እቅዱን ይፋ አደረገ
በጀቱ በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት የተጎዱ የአውሮፓ ጦር መሳሪያ ክምችትን ለማሳደግ ይውላል ተብሏል
የጦር መሳሪያ ግዢው በሀገራት መካከል ፉክክር በማያመጣ መንገድ ይከናወናል ተብሏል
የአውሮፓ ህብረት የ70 ቢሊዮን ዩሮ ጦር መሳሪያ ግዢ እቅዱን ይፋ አደረገ፡፡
የሩሲ እና ዩክሬን ጦርነት የዓለም የምግብ አና መድሃኒት ዋጋን ብቻ ሳይሆን የጦር መሳሪያ ፍላጎትንም እንዲጨምር አድርጓል፡፡
በተለይም የአውሮፓ ሀገራት ዩክሬን ከሩሲያ እየደረሰባት ያለውን ጥቃት እንድትመክት በሚል ያሏቸውን የጦር መሳሪያዎች ለዩክሬን በመርዳት ላይ መሆናቸው የጦር መሳሪያ ክምችታቸውን ጥያቄ ውስጥ አስገብቶታል፡፡
ይሄን የተረዳው የአውሮፓ ህብረት የአባል ሀገራቱን የጦር መሳሪያ መጠን ለማሳደግ የግዢ እቅድ ማዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች በብራስልስ እየመከሩ ሲሆን አዲስ የጦርመሳሪያ ግዢ እቅድ ይፋ አድርገዋል፡፡
በፈረንጆቹ 2025 ይተገበራል የተባለው ይህ እቅድ የ70 ቢሊዮን ዩሮ የጦር መሳሪያ ግዢ እንደሚካሄድ የአውሮፓ ህብረት ውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ኮሚሽነር ጆሴፕ ቦሬል ተናግረዋል፡፡
እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ የጦር መሳሪያ ግዢው የኮሮና ቫይረስ ክትባት ግዢ ላይ እንደተደረገው በአባል ሀገራቱ መካከል ፉክክር እና እሽቅድምድም በሌለበት መንገድ እንደሚሆንም ተገልጿል፡፡
ከሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ወይም ኔቶ አባል ሀገራት መካከል አሜሪካ ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ድጋፍ ካደረጉ መካከል ቀዳሚዋ ስትሆን ከዓመታዊ እድገታቸው አንጻር ግን የምስራቅ አውሮፓ ሀገራት ብዙ የጦር መሳሪያ መስጠታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በዚህም ምክንያት በርካታ የአውሮፓ ህብረት ሀገራት ያላቸውን ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች ለዩክሬን መስጠታቸውን ተከትሎ የጦር መሳሪያ ለመግዛት እየተገደዱ ይገኛሉም ተብሏል፡፡