የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ከጀርመን መራሄ መንግሥት ጋር ወደ ቤጂንግ ለመጓዝ ጥያቄ ቢያቀርቡም ጀርመን ጥያቄውን ውድቅ አድርጋለች
“ቻይና የአውሮፓ ዋነኛ ጠላት ነች” ሲል የአውሮፓ ህብረት አሳሰበ።
የአውሮፓ ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚዋ ጀርመን ከቻይና ጋር ያላትን የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስሯን ማጠናከሯን ተከትሎ ትችቶችን እያስተናገደች ትገኛለች።
የጀርመን ዋነኛ የኢኮኖሚ ኮሪደር የሆነው ሀምቡርግ ወደብ የ25 በመቶ ድርሻውን ለቻይናው መንግስታዊ ኮስኮ የሎጅስቲክስ ኩባንያ ለመሸጥ ማሰቡ በርሊን ላይ እየደረሰ ላለው ትችት ዋነኛው ምክንያት ነው።
ከሰሞኑ ደግሞ የጀርመን መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ቻይናን እንደሚጎበኙ መናገራቸውን ተከትሎ የአውሮፓ ሀገራት እየተቃወሙ ነው።
የአውሮፓ ህብረት የኢንዱስትሪ ኮሚሽነር ቴሪ ብሬቶን እንዳሉት ቻይና የአውሮፓ ሀገራት ኢንዱስትሪዎች ዋነኛ ጠላት መሆኗን ተናግረዋል።
የአውሮፓ መንግስታት እና ኩባንያዎች ቻይና ወነኛ ጠላት መሆኗን ተረድተው ከቤጂንግ ጋር የሚደረጉ የኢንቨስትመንት ትብብሮችን በትኩረት እንዲመለከቱም ኮሚሽነሩ አሳስበዋል።
ባለፉት ዓመታት የአውሮፓ ህብረት በተለይም የቻይና መንግሥት ኩባንያዎች ወደ ህብረቱ አባል ሀገራት ገብተው ጉዳት እንዳያስከትሉ ሲከላከል መቆየቱንም ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።
ጀርመን የአውሮፓ ህብረት የመከላከል እቅድን ወደ ጎን በማለት ከቻይና መንግሥት እና ኩባንያዎች ጋር አዳዲስ ስምምነቶችን ለመፈጸም ማሰባቸው የአውሮፓ ዲፕሎማቶችን እና መሪዎችን አስገርሟል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
ኮሚሽነሩ አክሎም ከሶስት ዓመት በፊት የአውሮፓ ህብረት ቻይናን በስትራቴጂክ ጠላትነት መፈረጁን ጠቁመዋል።
የጀርመን መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ህብረቱ ያሳለፈውን ይሄንን ውሳኔ ወደ ኋላ በማለት ቻይናን ለመጎብኘት ያቀዱ የመጀመሪያው የአውሮፓ መሪ እንደሆኑ ተጠቅሷል።
የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የጀርመን አቻቸውን የቻይና ጉብኝት የተቃወሙ ሲሆን በርሊን የአውሮፓን ንብረቶች ለቤጂንግ እንዳትሸጥ ጠይቀዋል።
ፕሬዝዳንት ማክሮን አክለውም አውሮፓ አለመከፋፈሉን ለማሳየት ከጀርመን አቻቸው ጋር ወደ ቤጂንግ አብረን እንጓዝ ቢሉም በርሊን ጥያቄውን ውድቅ አድርጋለች።