የአሜሪካ ወታደሮች አይኤስን ለመወጋት በሶሪያ እንዲቆዩ ተሰናባቹ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ጠየቁ
አዲሱ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በውጭ ጉዳይ ፖሊሲው በውጭ ሀገራት የሚገኙ ወታደሮችን ለማስወጣት አቅዷል
በአሁኑ ወቅት በሶሪያ ከ8-10 ሺህ የሚጠጉ የአይኤስ ታጣቂዎች እንደሚገኙ ይገመታል
አይኤስአይኤስ ታጣቂ ቡድን መልሶ እንዳይቋቋም አሜሪካ በሶሪያ ውስጥ ወታደሮቿን ማቆየት እንደሚኖርባት ተሰናባቹ የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስተን ተናገሩ፡፡
የበሽር አሳድ መንግስት ከስልጣን መወገዱን ተከትሎ ቡድኑ ሊጠናከር የሚችልበት እድል መኖሩ ለቀጠናው እና ለዋሽንግተን ትልቅ ስጋት ነው ብለዋል የመከላከያ ሚኒስትሩ፡፡
ሎይድ ኦስተን ከስልጣን ከመነሳታቸው በፊት ከአሶሼትድ ፕረስ ጋር ባደረጉት የመጨረሻ ቃለ መጠይቅ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የቀድሞ የአይኤስ ተዋጊዎች እና ቤተሰቦቻቸው የሚገኙባቸው የማቆያ ካምፖች ደህንነት ለማረጋገጥ የአሜሪካ ወታደሮች በስፍራው ሊቆዩ ይገባል ብለዋል፡፡
በአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር መስርያ ቤት ፔንታጎን መረጃ መሰረት በአሁኑ ወቅት በካምፕ ውስጥ 8-10 ሺህ የሚደርሱ የአይኤስ ተዋጊዎች እንደሚገኙ ከነዚህ መካከል 2 ሺህ የሚሆኑት በጣም አደገኛ ናቸው ተብሎ ይታሰባል።
ሚኒስትሩ “ሶሪያን ያለምንም ጥበቃ የምንተዋት ከሆነ ቡድኑ ወደ ዋና ስጋትነት የመመለስ እድሉ ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ እስካሁን ታጣቂዎችን ለመዋጋት የተደረገውን ጥረት ወደ ኋላ የሚመልስ ነው” ብለዋል፡፡
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያው የስልጣን ዘመናቸው በ2018 የአሜሪካ ወታደሮችን ሙሉ ለሙሉ ከሶሪያ ለማስወጣት እንቅስቃሴ ጀምረው ነበር፡፡
ባለፈው ወር የሃያት ታህሪር አል ሻም ቡድን (ኤች ቲ ኤስ) በአሳድ ላይ ሰፊ የውጊያ ዘመቻ ሲከፍት ትራምፕ የአሜሪካ ጦር ግጭት ካለባቸው የውጭ ሀገራት መውጣት እንደሚኖርበት ተናግረዋል፡፡
“ቅድሚያ ለአሜሪካ” በሚለው መርሀቸው በአዲሱ አስተዳደራቸውም በውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው ሶሪያን ጨምሮ በሌሎች የውጭ ሀገራት የሚገኙ ወታደሮችን ወደ ሀገር ቤት እንደሚመልሱ ይጠበቃል፡፡
በመካከለኛው ምስራቅም ሆነ በሌሎች ቀጠናዎች የሚታዩ የሽብርተኝነት እንቅስቃሴዎችን መግስታት ሃላፊነት የአሜሪካ ብቻ ሊሆን አይገባም የሚሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ሌሎች ቀጠናዊ ድርጅቶች እና ምዕራባውያን ሀገራት ለተልዕኮዎቹ በገንዘብ ፣ በጦር መሳሪያ እና በወታደሮች መዋጮ ከዚህ በተሻለ እንዲሳተፉ ጠይቀዋል፡፡
አይ ኤስ ሰፊ የሶሪያ ግዛትን መቆጣጠሩን ተከትሎ ከ2015 ጀምሮ በሶሪያ የአሜሪካ ወታደሮች የተሰማሩ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በስፍራቸው የሚገኙ ጦር አባላት ቁጥራቸው 2 ሺህ ይጠጋል፡፡