የአውሮፓ ህብረት እና ኢትዮጵያ ከፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በኋላ ግንኙነታቸው መሻሻሉ ይታወሳል
የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ 43 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ እንደሚሰጥ አስታወቀ።
የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመርዳት 43ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ ወይም 2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር እንደሚሰጥ አስታውቋል።
የህብረቱ የኢትዮጵያ ቢሮ ለአልዐይን እንዳስታወቀው የገንዘብ ድጋፉ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በግጭት እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመደገፍ የሚውል ነው።
ከዚህ በተጨማሪም ተፈናቃዮች በተጠለሉባቸው ያሉ ማህበረሰቦችን ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጿል።
የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ ድጋፍ ከሚያደርጉ ዓለም አቀፍ አጋሮች መካከል ዋነኛው መሆኑ ይታወሳል።
ህብረቱ በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2023 ዓመት 82 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ ወይም 4 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ለኢትዮጵያ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ተቀዛቅዞ የቆየ ሲሆን በፌደራል መንግሥት እና ትግራይ ሀይሎች መካከል በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ግንኙነታቸው እየተሻሻለ መጥቷል።
የቀድሞ ታጣቂዎችን ወደ ሰላማዊ ህይወያቸው ለመመለስ የተቋቋመው ብሔራዊ የተሀድሶ ኮሚሽን ከአውሮፓ ህብረት የ12 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ እንደሚደረግለት ኮሚሽነር ተሾመ ቶጋ ከሁለት ሳምንት በፊት መናገራቸው ይታወሳል።
በኢትዮጵያ በጦርነት፣ግጭቶች እና የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያቶች አስቸካይ ድጋፍ የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር ከ4 ሚሊዮን በላይ ደርሷል።