ሩሲያ በምክትል ፕሬዝደንት ካማላ ሃሪስ እና በሌሎች 28 የአሜሪካ ባለስልጣናት ላይ ማእቀብ ጣለች
ሩሲያ በምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ እና በሌሎች 28 የአሜሪካ ባለስልጣናት ፣ የንግድ ሰዎች እና ጋዜጠኞች ላይ ተጨማሪ የመግቢያ እገዳዎችን መጣሏን አስታውቃለች።
በሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የታተመው የማዕቀብ ዝርዝር የፌስቡክ መስራች ማርክ ዙከርበርግ፣ ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር ካትሊን ሂክስ እና የፔንታጎን ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ይገኙበታል።
"እነዚህ ግለሰቦች ላልተወሰነ ጊዜ ወደ ሩሲያ ፌዴሬሽን እንዳይገቡ ተከልክለዋል" ሲል የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው ገልጿል።
በዚሁ ቀን የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የካናዳ አስተዳደር የሩሲያ ፍራቻን ወይም ሩሶፎቢክን ይደግፋሉ ባላቸውን 61 የካናዳ ባለስልጣናት፣ ጋዜጠኞች እና ወታደራዊ ባለሙያዎች ላይ ማዕቀብ ጥሏል።
የልዩ ኦፕሬሽን ሃይሎች አዛዥ ሜጀር ጀነራል ስቲቭ ቦይቪን፣ የማዕከላዊ ባንክ ገዥ ቲፍ ማክሌም እንዲሁም የቶሮንቶ እና ኦታዋ ከንቲባ የሆኑት ጆን ቶሪ እና ጂም ዋትሰንን ጨምሮ 61ቱ ግለሰቦች ላልተወሰነ ጊዜ ወደ ሩሲያ እንዳይገቡ መደረጉን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
ሩሲያ ጎረቤቷ ዩክሬን ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከፈረንጆች የካቲት 24፤ 2022 ጀምሮ ወታደራዊ ዘመቻ ማካሄድ መጀመሯ ይታወቃል።
በየሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ከ5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሀገራቸውን ለቀው ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል፡፡ ሩሲያ በዩክሬን ላይ እየወሰደች ያለውን ወታደራዊ እርምጃ ከጀምሩም ቢሆን የተቃወሙት ምዕራባውያን፤ ሩሲያን ያዳክማሉ ያሉዋቸው ማዕቀቦች ሲጥሉ እየተስተዋሉ ነው።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ጠቅላላ ጉባኤ ባደረገው ስብሰባ ሩሲያ ዩክሬንን መዉረሯን የሚያወግዘዉን የዉሳኔ ሀሳብ በአብላጫ ድምጽ ማጸደቁም እንዲሁ የሚታወስ ነው።
የተመድ ጠቅላላ ጉባኤም ሩሲያ ተመድ የሰብአዊ መብት ምክርቤት በአብላጫ ድምጽ እንድትታገድ ያደረገ ሲሆን ሩሲያም ይህን ተከትሎ ከም/ቤቱ አባልነት መውጣቷን ማስታወቋ ይታወሳል፡፡
ሩሲያ ከም/ቤቱ የታገደችው ሩሲያ ጦር በዩክሬን ባካሄደው ጦርነት፣በሰብአዊነት ላይ ወንጅል ፈጽሟል በሚል ነበር፡፡