ጀርመን በአውሮፓ ግዙፍ ሆነ የታጠቀ ጦር ለመገንባት ዝግጁ መሆኗን ገለጸች
የጀርመኑ መሪ ኦላፍ ሾልዝ የአውሮፓ ሀገራት በኔቶ ጥላ ስር ሆነው ኃላፊነታቸው እንዲወጡ አሳስበዋል
የሩስያ-ዩክሬን ጦርነት ጀርመን የመከላከያ ፖሊሲዋን እንድትለውጥ አስገድዷል
የጀርመኑ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ ሀገራቸው የአውሮፓን ጸጥታ ለመምራት የሚያችላት ግዙፍ ሆነ የታጠቀ ጦር ለመገንባት ዝግጁ ነች አሉ፡፡
ኦላፍ ሾልዝ፤ በሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣኖች ፊት ባደረጉት ንግግር "ጀርመን ከፍተኛ የኢኮኖሚ አቅም ያላትና በአህጉሪቱ መሃል ያለች ሀገር እንደመሆኗ፤ ሰራዊታችን በአውሮፓ ውስጥ የመደበኛ መከላከያ የማዕዘን ድንጋይ መሆን አለበት” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
የሩስያ-ዩክሬን ጦርነት ፤ ጀርመን በመከላከያ ፖሊሲዋ ላይ ለውጥ በማድረግ ጦሯን ይበልጥ ለማጠናከር የ100 ቢሊዮን ዩሮ ልዩ ተጨማሪ ፈንድ ለማድረግ ያስገደደ መሆኑ ይታወቃል፡፡
የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትር ጀርመን በወዳጆቿ የተከበበች ሀገር ናት የሚል የተሳሳተ እምነት እንደነበራቸው ያነሱት ኦላፍ ሾልዝ፤ ጀርመን ከራሷ አልፎ የአውሮፓን ደህንነት የሚያረጋጋ ጦር የመገንባቷ ጉዳይ ግድ መሆኑም አንስተዋል፡፡
"ጀርመን ለአህጉራችን ደህንነት የመሪነት ሀላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን በግልጽ እና በታማኝነት እያሳየን ነው" ብለዋል ኦላፍ ሾልዝ።
ኦላፍ ሾልዝ፤ የአውሮፓ ሀገራት በሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ጥላ ስር ሆነው የበለጠ ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።
"እኛ አውሮፓውያን በኔቶ ውስጥ የበለጠ ሀላፊነት መውሰድ አለብን፤ ዘመናዊ እና ብቃት ያለው ጦር ያሏቸው ሁለቱ የአውሮፓ ሀገራት ፊንላንድ እና ስዊድን በቅርቡ ወደ ኔቶ መቀላቀላቸው በጣም ጥሩ ነው" ማታቸውም ዩሮ ኒውስ ዘግቧል፡፡
ኦላፍ ሾልዝ ባለፈው አመት በአፍጋኒስታን እንደነበረው እንደ ኢራቅ ፣ ማሊ እና ኒጀር በመሳሰሉና የአውሮፓ ምክር ወይም የስልጠና ተልእኮዎችን የሚያስፈልጋቸው ሀገራት ላይ ተልእኮዎችን ለመወጣት የሚያስችሉ “የአውሮፓ ዋና መስሪያ ቤቶች” ማቋቋም እንደሚደግፉም ተናግረዋል፡፡
ለዩክሬን ወታደራዊ ድጋፍ ለመላክ ዘግይተዋል ተብለው ሲተቹ የነበሩት የጀርመኑ መራሄ መንግስት፤ አሁን ላይ ለኪቭ የሚያደርጉት ድጋፍ አጠናክረው መቀጠላቸው የሚታወቅ ነው፡፡
የጀርመን መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ ሀገራቸው ለዩክሬን አዲስ የጦር መሳሪያ ልታበረክት መሆኑን እና በቅርቡ እንደሚላክላት መናገራቸውም ይታወሳል።
ኦላፍ ሾልዝ ሃምሌ ላይ በዩክሬን ጉብኝት ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን ሀገራቸው ዩክሬንን ለማገዝ ዝግጁ መሆኗን ለፕሬዝዳንት ዘለንስኪ መግለጻቸውም አይዘነጋም፡፡