ከጆ ባይደን ጋር ሲመክሩ የነበሩት የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከቻይናና ሩሲያ መሪዎች ጋር ሊነጋገሩ ነው
የሩሲያ፤ ሕንድና ቻይና መሪዎች ከዩክሬን ሩሲያ ጦርነት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊወያዩ ነው
መሪዎቹ የሚወያዩት በበይነ መረብ እንደሆነ ተገልጿል
የሩሲያ፤ ሕንድና ቻይና መሪዎች ከዩክሬን ሩሲያ ጦርነት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊወያዩ መሆኑ ተገልጿል፡፡
መሪዎቹ የሚገናኙት ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይናና ደቡብ አፍሪካ የተካተቱበትና ብሪክስ በመባል በሚጠራው ስብስባ ጉባዔ ላይ እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡ በዚህም መሰረት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂን ፒንግ እና የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ናቸው፡፡
መሪዎቹ በበይነ መረብ የሚገናኙት የቡድን ሰባት አባል ሀገራት ውይይት ከመደረጉ በፊት ነው ተብሏል፡፡ ቭላድሚር ፑቲን፣ ሺ ጂን ፒንግ እና ናሬንድራ ሞዲ ይወያያሉ ተብሎ የሚጠበቀው በፈረንጆቹ ሰኔ 24 ቀን ነው፡፡ ይህ ስብሰባ ከተደረገ ከሁለት ቀናት በኋላ የቡድን ሰባት ሀገራት ስብሰባ በጀርመን እንደሚደረግ መርሃ ግብር ወጥቷል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ወደ እስያ ባመሩበት ወቅት ከሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲንና ሌሎች መሪዎችን ማነጋገራቸው ይታወሳል ፡፡ ከሩሲያ እና ቻይና ፕሬዝዳንቶች ጋር እንደሚገናኙ የሚጠበቁት ናርንድራሞዲ ‘ኳድ’ በሚለው የአሜሪካ፣ ጃፓንና አውስትራሊያ ስብስብ ሀገራቸውን ማስገባታቸውና መወያየታቸው ይታወሳል፡፡
ከአሜሪካ ፕሬዝዳንትና ከሌሎች መሪዎች ጋር በመሆን ሩሲያ እና ቻይናን በሚመለከት አስተያየት ሲሰጡና ሲያስጠነቅቁ የነበሩት የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር አሁን ደግሞ በበይነ መረብ ፑቲንን እና ሺ ጅንፒንግን ሊያገኙ ነው፡፡
ቻይና፣ ሩሲያ እና ሕንድ በዓለም ጸጥታ ማዕቀፍ ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡