የሩሲያና ቻይና ጦር አውሮፕላኖች የእስያ ፓስፊክ አካባቢን እየቃኙ እንደሆነም ገልጸዋል
ቻይና እና ሩሲያ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በጎበኙት የአሲያ ክልል ላይ ወታደራዊ ልምምድ ማድረጋቸው ተገለጸ።
ቤጅንግ እና ሞስኮ ወታደራዊ ልምምድ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ተገልጿል።
ሀገራቱ ወታደራዊ ልምምዱን ያደረጉት የእስያ ፓስፊክ ቀጠናን ለመጠበቅና ቅኝት ለማድረግ መሆኑ እየተገለጸ ነው። ይህ የሀገራቱ ወታደራዊ ልምምድ የተደረገው ጆ ባይደን ከጎበኙት በኋላ መሆኑ እያነጋገረ ነው።
ሁለቱ ሀገራት ልምምዱን ያደረጉት ኳድ በሚል የተሰባሰቡትን ሀገራት ማለትም አሜሪካን፣ አውስትራሊያን፣ ጃፓንንና ህንድን ለመቀናቀን እንደሆነም እየተገለጸ ነው።
ደቡብ ኮሪያ ከሞስኮ እና ቤጅንግ ወታደራዊ ልምምድ በኋላ መግለጫ አውጥታለች። ሴኡል በመግለጫዋ ሁለት የቻይና እንዲሁ አራት የሩሲያ የጦር አውሮፕላኖች የአየር መከላከያ መለያ ዞኗ ውስጥ መግባታቸውን አስታውቃለች።
ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖቹ በጃፓን ባህር አካባቢ አድርገው ወደ ምስራቅ ቻይና ባህር ከዛም እስከ ፊሊፒንስ ባህር ድረስ ሲበሩ እንደነበር ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የአሜሪካ ባለስልጣን ተናግረዋል።
ጃፓን ተዋጊ ጀቷን በመላክ ቅኝት ማድረጓን ስትገልጽ ደቡብ ኮሪያ ደግሞ መከላከል የሚያስችል ቅኝት ማድረጉን አስታውቃለች።
ሀገራቱ ከዩክሬን ጦርነት በኋላ የመጀመሪያቸውን የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ማድረጋቸውን ያስታወቀው የቻይና መከላከያ ሚኒስቴር ነው። የተደረገው የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ሩሲያ በዩክሬን ወታደራዊ ዘመቻ ከደረገች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ራስን ለመከላከል የተደረገ እንደሆነም ቤጅንግ አስታውቃለች።
ሀገራቱ በ2019፣ 2020 እና 2021 ``ራስን መከላከል`` በሚል ዓላማ ወታደራዊ ልምምድ ሲያደርጉ እንደነበር ተገልጿል።
ሩሲያ የካቲት 24 በዩክሬን ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ መጀመሯን ተከትሎ ከምዕራባውያን ሀገራት ከፍተኛ ማዕቀብ ሲገጥማት፤ በቤጂንግ በበኩሏ ሁለቱም ወገኖች ወደ ሰላማዊ ድርድር እንዲመጡ ስታሳስብ መቆየቷ ይታወሳል።