በአፍሪካ ቀንድ እና በታላላቅ ሀይቆች አካባቢ ሰላም ለማምጣት የኬንያ ሚና አስፈላጊ ነው ሲል የአውሮፓ ህብረት ገለጸ
ኬንያ በቀጣናው ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ሚና እየተጫወተች ያለች ሀገር መሆኗ ይነገራል
ቻርለስ ሚሼል፤ ኬንያ ለቀጠናው ሰላም በምታደርገው ጥረት የአውሮፓ ህብረት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል
በአፍሪካ ቀንድ እና በታላላቅ ሀይቆች አካባቢ መረጋጋትን ለማስፋፋት የኬንያ አመራር ሚና አስፈላጊ መሆኑ የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቻርለስ ሚሼል ገለጹ፡፡
በ36ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ በአህጉሪቱ መዲና አዲስ አባባ የሚገኙት ፕሬዝዳንቱ ከኬንያው ፕሬዝዳንት ጋር የጎንዮሽ ውይይት አድርገዋል፡፡
ኬንያ ከ10 አመታት በኋላ ከሶማሊያ ጋር የሚያዋስናትን የማንዴራ ድንበር ልትከፍት ነው
መሪዎቹ በውይይታቸው የቀጣናውን ሰላምና ደህንነት በሚረጋገጥበት ሁኔታ እንዲሁም ኬንያ ልትጫተው ስለሚገባ ሚና አንስተው መክረዋል፡፡
የአውረፓ ህብረት ምክር ቤት ፕሬዝዳንቱ፤ በአሸባሪዎች እየተፈተነ ያለውን የአፍሪካ ቀንድም ሆነ በታላላቅ ሐይቆች ቀጠና (ግሬት ሌክስ) የሚፈገውን መረጋጋት ለማስፈን የኬንያ ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተናግረዋል፡፡
ኬንያ በምታደርገው ጥረት “የአውሮፓ ህብረት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደረግ ለፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ አረጋግጬላቸዋለሁ”ም ብለዋል ቻርለስ ሚሼል በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፋቸው፡፡
የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ሰላም እንደሚጣ ኬንያ ኃላፊነቷን ትወጣለች ሲሉ ከወራት በፊት ከፍራንስ-24 ጋር በነበራቸው ቆይታ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
ፕሬዝዳንቱ በዓለ ሲመታቸው ባከበሩበት ወቅት በኢትዮጵያ እና በታላላቅ ሐይቆች ቀጠና (ግሬት ሌክስ) ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ጥረት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሚያከናውኑትን ተግባር እንደሚቀጥሉ መናጋራቸው ይታወሳል።
በተለይም የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት መቋጫ እንዲያገኝና አሁን የተደረሰውን ስምምነት እውን እንዲሆን በማድረግ በኩል ኬንያ ትልቅ ድርሻ መጫወቷ ይታወቃል፡፡
በዚህም ኬንያ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እያበረከተች ያለውን አስተዋጽኦ በአሜሪካ እና አውሮፓ ህብርት ትልቅ አድናቆት ሲቸረው ይስተዋላል፡፡
የአሜሪካው ከፍተኛ ዲፕሎማት አንቶኒ ብሊንክን በቅርቡ ከኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ጋር በነበራቸው ቆይታ ይህንኑ የኬንያን ጥረት ማድናቃቸውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት መግለጹም ይታወሳል፡፡
ኬንያ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ተይዞ የነበረውን የቀጠናውን የዲፕሎማሲ ሚና እየወሰደች ያለች ሀገር እንደሆነች ይነገራል፡፡