የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኬንያ የሁለት ቀናት ጉብኝታቸውን አጠናቀዋል
ኬንያ በአስመራ ኢምባሲዋን እንደምትከፍት ገለጸች፡፡
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከትናንት ጀምሮ ኬንያን በመጎብኘት ላይ ናቸው፡፡
ፕሬዝዳንቱ በናይሮቢ የሁለት ቀናት ቆይታቸው ከኬንያ አቻቸው ዊሊያም ሩቶ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች መምከራቸውን የሀገሪቱ መረጃ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል በትዊትር ገጻቸው ላይ ጽፈዋል፡፡
የሁለቱ ሀገራት ፕሬዝዳንቶች በሁለትዮሽ እና አካባቢያዊ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውን ያነሱት ሚኒስትሩ ከዛሬ ጀምሮም የሁለቱ ሀገራት ዜጎች ያለቪዛ እንዲንቀሳቀሱ መስማማታቸውን አክለዋል፡፡
በዚህ ስምምነት መሰረትም ኬንያዊያን ያለ ቪዛ ወደ ኤርትራ እንዲሁም ኤርትራዊያን ወደ ኬንያ ያለቪዛ መንቀሳቀስ ይችላሉም ተብሏል፡፡
ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ኬንያ በኤርትራ መዲና አስመራ ኢምባሲዋን እንደምትከፍት ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ መናገራቸውንም ሚኒስትሩ አክለዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ሩቶ ከሶስት ሳምንት በፊት ወደ አስመራ ተጉዘው ከኤርትራ አቻቸው ጋር መክረው መመለሳቸው አይዘነጋም፡፡
ኢትዮጵያ እና ኬንያ ዜጎቻቸው በተመሳሳይ ያለ ቪዛ አንዳቸው ወደ ሌላኛው ሀገር እንዲንቀሳቀሱ መስማማታቸው ይታወሳል፡፡