አውሮፓ ከዩክሬናዊያን ጎን መሆኑን እንዲያረጋግጥ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ጠየቁ
የአውሮፓ ፓርላማ ዩክሬን የአውሮፓ ህብረት አባልነት የውሳኔ ሀሳብን ደግፏል
ፕሬዘዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ የአውሮፓ ህብረት ዩክሬንን በልዩ ሁኔታ በአባልነት እንዲቀበል ጠይቀዋል
አውሮፓ ከዩክሬናዊያን ጎን መሆኑን እንዲያረጋግጥ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ጠየቁ።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦርን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ በተፈጠረ አለመግባባት ከሩሲያ ጋር ወደ ጦርነት ያመሩ ሲሆን ጦርነቱ ከተጀመረ ዛሬ ስድስተኛ ቀናቸው ላይ ናቸው።
የዩክሬኑ ፕሬዘዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ከቀናት በፊት አሜሪካ እና የአውሮፓ ሀገራት በሩሲያ ላይ እርምጃዎችን እንዲወስዱ አሳስበው ዩክሬን የአውሮፓ ህብረት አባልነትን በልዩ ሁኔታ እንዲቀበልም ጠይቀው ነበር።
የህብረቱ ፓርላማም በዛሬው ዕለት ከዩክሬን በቀረበለት የአባልነት ጥያቄ ዙሪያ በብራስልስ ተወያይቶ የወሳኔ ሀሳቡን አጽድቋል።
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪም በበይነ መረብ ታግዘው ለፓርላማ አባላቱ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፤ አውሮፓዊያን ከዩክሬን በኩል መሆናቸውን ሊያሳዩን ይገባል ሲሉ ንግግር አድርገዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም ዩክሬን ብቻዋን ሩሲያን እየተዋጋች ነው፣ የምንዋጋው እኩልነታችንን ለማሳየት ነው፤ አውሮፓዊያን ሊያግዙን የግባል ሲሉም ለህብረቱ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ምክትል ፕሬዝዳንት ማሮስ ሴፍኮቪች በበኩላቸው፤ በዩክሬኑ ፕሬዘዳንት “ከእኛ ጎን መሆናችሁን የህብረቱ አባል ሀገር አድርጋችሁ አረጋግጡልን” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ “ከእናንተ ጋር ነን” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ከዩክሬን ድል በኋላም ሀገራችሁን በጋራ እንገነባታለን ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ የህብረቱ አባል ሀገር ለመሆን የቀረበው ጥያቄ ምላሽ በመሰጠት ላይ መሆኑንም አክለዋል፡፡
ሩሲያ እና ዩክሬን የገቡበትን አለመግባባት በውይይት ለመፍታት በቤላሩስ ትናንት የመከሩ ቢሆንም ስምምነት ላይ ስለመድረሳቸው እስካሁን በይፋ የተገለጸ ነገር ባይኖርም ውይይታቸውን ከሁለት ቀን በኋላ ዳግም ለመጀመር ተስማምተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን የዩክሬን መዲና ኬቭን ለመቆጣጠር የሩሲያ ወታደሮች በውጊያ ላይ ሲሆኑ በሩሲያ ላይ የሚጣሉ ማዕቀቦች ግን እንደቀጠሉ ናቸው።
ሩሲያ በበኩሏ ዩክሬናዊያን ራሳቸውን ከደህንነት ተቋማት አካባቢዎች እንዲያርቁ ያስጠነቀቀች ሲሆን የሩሲያ ብረት ለበስ የጦር ተሸከርካሪዎችን ወደ ዩክሬን ዋና ከተማ በመትመም ላይ መሆናቸውን የሳተላይት መረጃዎች ያስረዳሉ።