በቤላሩሱ ድርድር ዩክሬን የሩሲያ ኃይሎች ከክሪሚያ ጭምር እንዲወጡ ጠየቀች
የሁለቱ ሀገራት ልዑካን በዩክሬንና ቤላሩስ ድንበር ተገናኝተው እየተደራደሩ ነው
ሩሲያ በዩከሬን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ማካሄድ ከጀመረች አምስት ቀናት ተቆጥረዋል
ዩክሬን ሩሲያ ከአመታት በፊት ይዛት ከነበረችው ክሪሚያ ግዛት ጭምር የሩሲያ ሃይሎች እንዲወጡ ጠይቃለች ተብሏል፡፡
ዩክሬን ይህንን ያለችው የዓለም አቀፉን ማህበረስብ ቀልብ የሳበውን ጦርነት ለማስቆም ከሩሲያ ጋር ለመደራደር በቤላሩስ በተቀመጠችበት መድረክ ነው፡፡
መረጃዎች እንሚያመላክቱት ከሆነ ዩክሬን ድርድሩ እውን እንዲሆን መጀመሪያ ቶክስ እንዲቆም እንዲሁም የሩሲያ ጦር ከተቆጣጠራቸው ወታደራዊ ይዞታዎች ለቆ እንዲወጣ ጠይቃለች፡፡
የዩክሬን ፕሬዝዳንት አማካሪ አሌክሰይ አርስቶቪች “ኬቭ በድርድሩ ወቅት የሩሲያ ወታደሮች ከክሬሚያ እና ዶንባስ ግዛቶች እንዲወጡ ስትል ጠይቃለች” ብለዋል።
ዜለንስኪ ትናንትና ሞስኮ እና ኬቭ በቤላሩስ ሳይሆን በሌላ ቦታ መነጋገር እንዳለባቸው ሲገልጹ ቢቆዩም፤ በኋላ ላይ ግን ያለቅድመ ሁኔታ ለመነጋገር መስማማታቸው ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎም ዛሬ የሁለቱ ሀገራት ልዑካን በዩክሬንና ቤላሩስ ድንበር ተገናኝተው እየተነጋሩ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
ዜለንስኪ፤ ቤላሩስ ሀገራቸው እንድትጠቃ ግዛቷንም ጭምር በመፍቀዷ ቤላሩስ ውስጥ ከሩሲያ ጋር የምንነጋገርበት ምክንያት የለም ማለታቸው አይዘነጋም።ይሁንና ፕሬዝዳንቱ በሰአታት ውስጥ ውሳኔያቸው ሊቀለብሱ ችሏል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በሰአታት ውስጥ የአቋም ለውጥ እንዴት አሰዩ ለሚለው በምክንያትነት የተቀመጠ ግልጽ ነገር ባይኖርም፤ የሩሲያ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ጥቃት የፈጠረው ተጽእኖ እንደሆነ እየተነገረ ነው።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ ለእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን የሚቀጥሉት 24 ሰዓታት እጅግ ወሳኝ ናቸው ማለታቸው ተሰምቷል
ሩስያ በዩከሬን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ማካሄድ ከጀመረች አምስት ቀናት ተቆጥሯል፡፡
ሩሲያ በዩክሬን ውስጥ የከፈተችውን ጦርነት ወታደራዊ ዘመቻ ብላ የሰየመችው ሲሆን አሜሪካን ጨምሮ ምእራባውያን ሀገራት ወረራ ነው በማለት የሩሲያን ጦርነት አውግዘዋል፡፡
አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ላይ መጠነ ሰፊ ማእቀብ ጥለዋል፤ ሩሲያ በአንጻሩ ተመሳሳይ እርምጃዎችን እየወሰደች ነው፡፡ በምእራባውያን ማእቀብ የተቆጡት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ፑቲን የኑክሊየር ጦራቸው በተጠንቀቅ እንዲቆም አዘዋል፡፡