ፕሬዝዳንቱ የኔቶ አባል ለመሆን ለ27ቱም የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ያቀረቡት ጥያቄ ሁሉንም አባል ሃገራት እንዳስፈራ ገልጸዋል
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌኒስኪ “ብቻችንን አጋፍጠውናል” ሲሉ ምዕራባውያንን ወቀሱ፡፡
ዜሌኒስኪ “ሃገራችንን ለመጠበቅ በብቸኝነት እየተዋጋን ያለነው እኛው ነን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
“ማን አግዞን ከጎናችን ሆኖ ተዋጋ?” ሲሉ የሚጠይቁት ፕሬዝዳንቱ “ማንም” ሲሉ ይመልሳሉ፡፡
የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ አባል ለመሆን የ27ቱንም የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት በር ማንኳኳታቸውን የሚናገሩም ሲሆን ሁሉም በጥያቄው መፍራታቸውን ይገልጻሉ፤ “እኛ ግን አልፈራንም” ሲሉ በማከል፡፡
“ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንደተወን ነው የተሰማኝ፤ እንደሚደግፉን ነበር ቃል ሲገቡልን የነበሩት፤ ሆኖም ሞትን እንድንጋፈጥ ብቻችንን ትተውናል” ሲሉም ነው ፕሬዝዳንቱ በዛሬ የቪዲዮ መልዕክታቸው የተናገሩት፡፡
ዜሌንስኪ ሃገራቸው ከሩሲያ ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል፤ ይህን ማለቷ በፍራቻ እንዳልሆነ በመጠቆም፡፡
ሩሲያ በቀላሉ ወደ ዩክሬን ዘልቃ ለመግባት የቻለችበት ጦርነት ሁለተኛ ቀኑን አስቆጥሯል፡፡ ጦርነቱ አሁንም በመካሄድ ላይ ሲሆን የሩሲያ ጦር ወደ ዩክሬን ዋና ከተማ ኪቭ ለመግባት መቃረቡ እየተነገረ ይገኛል፡፡
ሩሲያ በዋናነት እርሳቸውንና ቤተሰባቸውን ዒላማ ማድረጓን የተናገሩት ዜሌኒስኪ የሩሲያ ጦር የልዩ ኃይል አባላት ወደ ከተማዋ መግባታቸውን በዛሬ ማለዳ መግለጫቸው ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡