የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ውሳኔውን አድንቀዋል
የአውሮፓ ፓርላማ ሩሲያን "የሽብርተኝነት ደጋፊ" በማለት ፈርጇል፡፡ ኃይሏም በዩክሬን ጦርነት አሰቃቂ ድርጊቶችን ፈጽሟል ብሏል።
የአውሮፓ ህግ አውጭዎች የወሰዱት እርምጃ ምንም አይነት ህጋዊ ውጤት የሌለው ተምሳሌታዊ የፖለቲካ እርምጃ ነው የተባለ ሲሆን፤ ነገር ግን 27ቱ የአውሮፓ ህብረት ሀገራት ይህን እርምጃ እንዲከተሉ አሳስበዋል።
"ሩሲያ ፌዴሬሽን በዩክሬን ንጹሀን ላይ ሆን ተብሎ የተፈጸመ ጥቃት እና ጭካኔ፣ የመሰረተ ልማቶች ውድመት እና ሌሎች ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሽብር ድርጊቶች ናቸው" ሲል በአውሮፓ ህብረት ህግ አውጭዎች የጸደቀው ውሳኔ ገልጿል።
ፓርላማው “ሩሲያን የሽብርተኝነት ደጋፊ እና የሽብርተኝነት መንገዶችን የምትጠቀም ሀገር እንደሆነች እውቅና ይሰጣል” ብሏል።
ኪየቭ ሩሲያን “በሀገሪቱ ላይ በወረራ ፈጽማለች” በሚል ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ "አሸባሪ" ብሎ እንዲያውጅ ስትጠይቅ ቆይታለች። የፓርላማው ውሳኔ ግን ሞስኮን ያስቆጣል ተብሏል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ውሳኔውን ማድነቃቸውን አል አረቢያ አጃንስ ፍራንስ ፕረስን ጠቅሶ ዘግቧል።
የአውሮፓ ህብረት ሀገራትን “የሽብርተኝነት ድጋፍ ሰጭ” ብሎ የሚፈርጅበት የህግ ማዕቀፍ የለውም ተብሏል።
ውሳኔው በ494 የም/ቤቱ አባላት የተደገፈ ሲሆን 58ቱ ደግሞ ተቃውመውታል።
ሩሲያ ሽብርተኝነትን የምትደግፍ ሀገር ብቻ ሳትሆን የሽብር ዘዴዎችን የምትጠቀም ናት ሲሉ የሊቱዌኒያ የም/ቤቱ አባል አንድሪየስ ኩቢሊየስ በማለት የውሳኔውን ግፊት መርተዋል።
በተለያዩ የምስራቅ አውሮፓ ሀገራት ህግ አውጭዎች የሩሲያን “ሽብርተኝነትን” ለማውገዝ ድምጽ ሰጥተዋል ተብሏል።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በየካቲት ወር ወታደሮቻቸው እንዲያጠቁ ካዘዙ በኋላ የአውሮፓ ህብረት በሞስኮ ላይ ዘይት ወደ ውጭ መላክ እንዳትችል እና ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ ያነጣጠረ ስምንት ዙር ታይቶ የማይታወቅ ማዕቀብ ጥሏል።