የአውሮፓ ሀገራት በሩሲያ ነዳጅ ዙሪያ ወደ ስምምነት መምጣት እንዳልቻሉ ተገለፀ
የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ነዳጅ ላይ የዋጋ ትመና ቢያወጣም ከአባል ሀገራት ተቃውሞ ገጥሞታል
ሩሲያ የአውሮፓ ሀገራት ነዳጄን ከፈለጋችሁ የጣላችሁብኝን ማዕቀብ አንሱ ስትል አስጠንቅቃለች
የአውሮፓ ሀገራት በሩሲያ ነዳጅ ዙሪያ ወደ ስምምነት መምጣት እንዳልቻሉ ተገለጸ።
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ስድስት ወራት ያለፈው ሲሆን ጦርነቱ በዓለም ምግብ እና ነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ እንዲመዘገብ ምክንያት ሆኗል።
ይህ በዚህ እንዳለም ጦርነቱ በዓለም ዲፕሎማሲ ላይ የተለያዩ መፋለሶችን ያስከተለ ሲሆን ሀገራት ከትብብር ይልቅ ጎራ ለይተው እንዲሰለፉ እያደረገም ይገኛል።
አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ላይ በተለያየ መንገድ በመሳተፍ ላይ ሲሆኑ በሩሲያ ላይ ከስድስት ሺህ በላይ ማዕቀቦችን ጥለዋል።
ሩሲያም የአጸፋ እርምጃ በመውሰድ ላይ ስትሆን ማዕቀቡ ለአውሮፓ ሀገራት የምታቀርበውን ጋዝ ሽያጭ እክል አስከትሏል።
ይሄንን ተከትሎም 40 በመቶ ለሚሆኑ የአውሮፓ ሀገራት ነዳጅ ስታቀርብ የነበረችው ሩሲያ በማዕቀቡ ምክንያት ለአውሮፓውያን ነዳጅ መላክ አለመቻሏን በተደጋጋሚ ገልጻለች።
የዓለማችን ሰባቱ ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆኑት የቡድን ሰባት አባል ሀገራት ከሰሞኑ በሩሲያ ነዳጅ ላይ የዋጋ ተመን ማውጣታቸው ይታወሳል።
እነዚህ ሀገራት ሩሲያ ነዳጇን በተተመነላት ዋጋ መሰረት ለአውሮፓ ሀገራት እንድትሸጥ የወሰኑ ቢሆንም ሩሲያ በበኩሏ ምንም አይነት ነዳጅ ወደ አውሮፓ አልሸጥም የሚል ውሳኔ አሳልፋለች።
የአውሮፓ ሀገራት የኢነርጂ ሚኒስትሮች በቤልጂየም መዲና ብራስልስ አስቸኳይ ስብሰባ የተቀመጡ ሲሆን የነዳጅ እጥረት ደግሞ ዋነኛው የስብሰባ መወያያ አጀንዳ ነበር፡፡
የአውሮፓ ህብረት ሩሲያ ነዳጇን በተቀመጠላት የወጋ ተመን እንድትሸጥ የወሰነውን ውሳኔ በዚህ ጉባኤው ላይ ያቀረበ ቢሆንም ውሳኔው በተቃውሞ እና በድጋፍ ታጅቧል፡፡
ለሩሲያ ቅርብ የሆኑት የምስራቅ አውሮፓ ሀገራት የአውሮፓ ህብረት ያቀረበውን አማራጭ የደገፉ ቢሆንም የተቀሩት የአውሮፓ ሀገራት ግን ህብረቱ ያስቀመጠው መፍትሄ ከነ ጭራሹ የነዳጅ እጥረቱን የሚያባብስ ነው በማለታቸው የብራስልሱ አስቸኳይ ጉባኤ ያለስምምነት ተጠናቋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ሩሲያ በበኩሏ የአውሮፓ ህብረት በሞስኮ ላይ የጣለውን ማዕቀብ ካላነሳ አንዲት ጠብታ ነዳጅ ወደ አውሮፓ አልክም በሚለው አቋሟ እንደጸናች ትገኛለች፡፡
በሩሲያ ውሳኔ የአውሮፓ ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆኑት ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ብሪታንያ፣ ቤልጂየም እና ሌሎች ሀገራት በነዳጅ ዕጥረት እየተፈተኑ ሲሆን ሰራተኞቻቸው የጠቃውሞ ሰልፍ በመውጣት ላይም ናቸው ተብሏል።