ህብረቱ የምርጫውን ሂደትና የምርጫ ቦርድን ስራ እንደሚደግፍ አስታውቋል
የአውሮፓ ህብረት ዛሬ ባወጣው መግለጫ ለምርጫ 2013 የታዛቢ ቡድን መላክ ባለመቻሉ መጸጸቱን አስታውቋል፡፡
ከወር በፊት ህብረቱ ለመታዘብ ያስችሉኛል ባላቸው ሁኔታዎች ዙሪያ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ባደረገው ውይይት አለመስማማቱን ገልጾ፣ የመታዘብ እቅዱን ማንሳቱን አስታውቆ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የአውሮፓ ህብረት ምርጫውን ለታዘብ ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች “ሉዓላዊነት ስለሚጋፉ” ስለሆኑ ህብረቱ ምርጫ ለመታዘብ ያስቀመጣቸውን ቅድመ ሁኔታ እንደማይቀበል ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት አቋሙን ካሳወቀ በኋላ ህብረቱ የምርጫው እለት ልኡክ እንደሚልክ አስታውቆ ነበር፡፡ ህብረቱ ዛሬ መግለጫው በድጋሚ ምርጫውን የሚታዘብ ልዑክ መላክ እንደማይችል እና በድርጊቱ ማዘኑን ገልጿል።
ከነገ በስቲያ ማለትም ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም የሚካሄደው ምርጫ ለኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ለውጥ ሂደት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው የገለጸው ህብረቱ በቀጣይ ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አብሮ እንደሚሰራ አስታውቋል።
አሁን ላይ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፤የፖለቲካ ውጥረቶች እና ሌሎች ውስብስብ ችግሮች አሉባት ያለው የህብረቱ መግለጫ በቀጣይ ሁሉን አቀፍ እና አሳታፊ ውየይቶች እንዲደረጉም አሳስቧል።
በኢትዮጵያ የሚካሄደውን የፖለቲካ ሽግግር እንደሚረዳ የገለጸው ህብረቱ የምርጫውን ሂደትና የምርጫ ቦርድን ስራ እንደሚደግፍ ገልጿል፡፡
በ6ኛው የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ምርጫ 45ሺ ታዛቢዎች ምርጫውን ለመታዘብ ፍቃድ መውሰዳቸውን የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡