ዓለም አቀፍ የምርጫ ታዛቢዎች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ነው
የአፍሪከ ህብረት እና የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሃይል የምርጫ ታዛቢዎች አዲስ አበባ ገብተዋል
ዘጠኝ ዓለም አቀፍ ተቋማት የምርጫ ታዛቢዎችን እንደሚልኩ መግለጻቸው ይታወሳል
ዓለም አቀፍ የምርጫ ታዛቢዎች የፊታችን ሰኞ ሰኔ 14 2013 ዓ.ም የሚካሄደውን ምርጫ ለመታዘብ ወደ አዲስ አበባ እየገቡ ነው።
እስካሁንም የአፍሪከ ህብረት እና የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሃይል የምርጫ ታዛቢዎች አዲስ አበባ መግባታቸው ታውቋል።
በቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንትና የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ሀላፊ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ የተመራ የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ትላንት ማምሻውን አዲስ አበባ ገብቷል።
የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሃይል ከአባል ሃገራቱ የተውጣጣ እና 28 አባላት ያሉት የምርጫ ታዛቢ ቡድኑን ወደ ኢትዮጵያ መላኩን አስታውቋል።
ታዛቡ ቡድኑ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ አፋር፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ክልል፣ ድሬ ዳዋ እና በአዲስ አበባ ተዘዋውሮ የምርጫውን ሁኔታ የሚከታተል መሆኑንም ባወጣው መግለጫ ገልጿል።
የምርጫውን ሂደት ለመታዘብ የመጡት ታዛቢዎቹ በቆይታቸው፤ ምርጫው ዴሞክራሲያዊና ዓለም አቀፍ የምርጫ መርሆዎችን ባከበረ መልኩ መካሄድ አለመካሄዱን እንዲሁም የምርጫውን ግልጽነትና ታማኝነት በመከታተል በምርጫው ሪፖርት የሚያቀርቡ ይሆናል።
የአሜሪካ እና የሩሲያ ሲቪል ማህበረሰብን ጨምሮ ዘጠኝ ዓለም አቀፍ ተቋማት ምርጫ የሚታዘቡ የባለሙያዎች ቡድን እንደሚልኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም መግለጹ ያታወሳል።
በዚህም መሰረት የአሜሪካ ኤምባሲ እና የብሪታንያ ኤምባሲ ዲፕሎማቶች፣ የሩሲያ ሲቪል ማህበረሰብ፣ የአፍሪካ ህብረት፣ የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ብርጌድ ቲም፣ መቀመጫቸውን አሜሪካ ያደረጉት 'ናሽናል ዴሞክራሲ' እና 'ኢሎክቶራል ኢንስቲትዩት ፎር ሰስቴኔብል ዴሞክራሲ ኢን አፍሪካ' የተባሉ ተቋማት ምርጫውን እንደሚታዘቡም ነው በወቅቱ የተገለጸው።
የአውሮፓ ህብረት ታዛቢዎችን እንደማይልክ ቢያስታውቅም የባለሙያዎች ቡድን እንደሚልክ በወቅቱ መግለጹም አይዘነጋም።