በኢትዮጵያ ያለው ችግር በሰላም እንዲፈታ ተመድ ፤ የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ ጠየቁ
የኢትዮጵያ መረጋጋት ለቀጣናው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው የተመድ ዋና ጸኃፊ አንስተዋል
ሕወሓት በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የጦር ሰፈሮች ላይ ጥቃት ማድረሱ እንዳሳሰባት አሜሪካ ገልጻለች
በኢትዮጵያ ያለው ችግር በሰላም እንዲፈታ ተመድ ፤ የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ ጠየቁ
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ፣ ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) በትግራይ ክልል በሚገኙ የኢትዮጵያ ብሄራዊ መከላከያ ሰራዊት የጦር ሰፈሮች ላይ ጥቅምት 24 ጥቃቶችን የማድረሱ ዜና አሜሪካን በጥልቅ እንዳሳሰባት ገልጿል፡፡
በዚህም ሳቢያ በአሳዛኝ ሁኔታ በተከሰተው የሰው ህይወት መጥፋት አሜሪካ ማዘኗን የገለጸው ሚኒስቴሩ ሰላምን በማስፈን ውጥረቶችን ለማርገብ የሚያስችሉ አስቸኳይ እርምጃዎች እንዲወሰዱ አሳስቧል።
የንጹኃንን ደህንነት መጠበቅ ያስፈልጋል ያለው መግለጫው ሚኒስቴሩ ሁኔታውን በጥብቅ መከተሉን እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም “አሜሪካ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን የቆመች ሲሆን ለሰላም ፣ ለብልፅግና ፣ ለዴሞክራሲ እና ለህግ የበላይነት ጽኑ አቋም ካላቸው አካላት ሁሉ ሁሉ ጋር ትሰራለች” ብሏል፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮም በትዊተር ገጻቸው ይህንኑ የሚመሩትን በስሪያ ቤት መግለጫ አጋርተዋል፡፡
በተመሳሳይ የተባበሩት መንግስታት (ተመድ) ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ፣ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ያለው ውጊያ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።
ዋና ጸኃፊው ውጥረቱ እንዲረግብና ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲገኝም ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን የኢትዮጵያ መረጋጋት ለአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ያለውን ሚና አስምረውበታል፡፡
የተባበሩት መንግስታት በኢትዮጵያ የሚካሔደውን የሪፎርም ጉዞ በቀጣናው ካሉ አጋሮቹ ጋር በመሆን መደገፉን እንደሚቀጥልም ነው ጉተሬዝ የገለጹት፡፡
ይህ ካልሆነ ሀገሪቱን ብቻ ሳይሆን ቀጣናውንም እንደሚያናጋው ነው ህብረቱ የገለጸው፡፡ የአውሮፓ ህብረትም እንዲሁ ሁኔታውን በመከታተል ላይ እንደሆነ እና ውጥሩ እንዲረግብ ጠይቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ትናንት በሰጡት መግለጫ ከሕወሓት ኃይል ጋር የሚደረገው ውጊያ መቀጠሉን አስታውቀዋል፡፡