የአውሮፓ ህብረት በኢራን የሚሳኤልና ድሮን አምራቾች ላይ ማዕቀብ ለመጣል ተስማማ
አሜሪካም በእስራኤል ላይ ጥቃት የፈጸመችውን ኢራን በማዕቀብ እቀጣለሁ ብሏለች
ምዕራባውያን እስራኤል ከኢራን ጋር የገባችበትን ፍጥጫ እንድታረግብ ጥሪ ማስተላለፋቸው ቀጥለዋል
የአውሮፓ ህብረት በኢራን የሚሳኤልና ድሮን አምራቾች ላይ ማዕቀብ ለመጣል ተስማማ።
27ቱ የህብረቱ አባል ሀገራት መሬኦች በብራሰልስ ከመከሩ በኋላ ነው በቴህራን ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ለመጣል ከስምምነት የደረሱት።
የህብረቱ ምክርቤት ፕሬዝዳንት ቻርለስ ሚሸል “ኢራንን ለማግለል የትኛውንም እርምጃ መውሰድ ወሳኝ” ነው ማለታቸውንም ሬውተርስ ዘግቧል።
የአውሮፓ ህብረት ኢራን ለሩሲያ ድሮኖችን በመሸጥ በዩክሬኑ ጦርነት ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው በሚል በርካታ ማዕቀቦችን መጣሉ ይታወሳል።
በትናንትናው እለት በኢራን ድሮን እና ሚሳኤል አምራች ኩባንያዎች ላይ ያነጣጠረ ማዕቀብ ለመጣል የወሰነውም ቴህራን ከ300 በላይ ድሮን እና ሚሳኤሎችን ወደ እስራኤል መተኮሷን ተከትሎ ነው።
የእስራኤል ዋነኛ አጋር አሜሪካም በቀጣይ ቀናት በኢራን ላይ አዲስ ማዕቀብ እንደምትጥል ይፋ አድርጋለች።
የኢራን ነዳጅ ለውጭ ገበያ እንዳይቀርብ ማድረግ፤ በኢራን የሚሳኤልና ድሮን ፕሮግራም እንዲሁም በሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር ላይ ማዕቀብ ለመጣል መታቀዱንም ነው የአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት አማካሪው ጃክ ሱሊቫኒ የተናገሩት።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች እስራኤል የአጻፋ እርምጃ ከወሰደች ውጥረት የበዛበት የመካከለኛው ምስራቅ የጦርነት ቀጠና ይለወጣል በሚል ቴል አቪቭን እያሳሰቡ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ግን “እስራኤል ራሷን ለመጠበቅ የሚያስችላትን ውሳኔ በራሷ ትወስናለች” ነው ያሉት።
ኔታንያሁ ከብሪታንያ እና የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ሲመክሩ” እስራኤል ራሷን ለመጠበቅ የትኛውንም እርምጃ ትወስዳለች” ማለታቸውን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
የብሪታንያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮንም እስራኤል ለኢራን የድሮን እና ሚሳኤል ጥቃት አጻፋውን ለመመለስ ሳትዘጋጅ እንዳልቀረች ተናግረዋል።
እስራኤል አጋሮቿ በኢራን የሚሳኤል ፕሮግራም ላይ ማዕቀብ እንዲጥሉና የኢራን አብዮታዊ ዘብን በሽብርተኛ ድርጅትነት እንዲመዘግቡ ጥሪ አቅርባለች።