የእስራኤል ጦር አዛዥ ሄርዚ ሀለቪ እስራኤል ኢራን ለፈጸመችው ጥቃት ምላሽ ትሰጣለች ብለዋል
የእስራኤል ጦር ለኢራን ጥቃት ምላሽ እሰጣለሁ ሲል ዛተ።
እስራኤላውያን ኢራን ለመጀመሪያ ጊዜ በእስራኤል ላይ ላደረሰችው ቀጥተኛ ጥቃት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ምን እንደሚሉ እየጠበቋቸው ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢራን ላደረሰችው የሚሳይል እና የድሮን ጥቃት ምላሽ በመስጠት ጉዳይ ከጦር ካቢኔያቸው ጋር በ24 ሰአታት ውስጥ ሁለት ጊዜ መሰብሰባቸውን ሮይተርስ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።
የእስራኤል ጦር አዛዥ ሄርዚ ሀለቪ እስራኤል ምላሽ ትሰጣለች ብለዋል። ነገርግን አዛዡ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።
"ወደ እስራኤል ግዛት በርካታ ሚሳይሎችን እና ድኖሮችን የማስወንጨፍ ተግባር ምላሽ ያስፈልገዋል" ሲሉ የተወሰነ ጉዳት ባጋጠመው እና በደቡብ እስራኤል በሚገኘው በነቫቲም የአየር ኃይል ቤዝ ተገኝተው ተናግረዋል።
የእስራኤል የበቀል እርምጃ ትወስዳለች የሚለው ግምት ከ2022-23 ጀምሮ በከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና ውስጥ ያሉትን ኢራናውያን ስጋት ውስጥ ከቷቸዋል።
ኢራን በእስራኤል ላይ የሚሳይል እና ድሮን ጥቃት ያዘነበችው በፈረንጆቹ ሚያዝያ አንድ በሶሪያ የሚገኘውን ኢምባሲዋን እንዳጠቃችባት በመግለጽ ነበር።
ምንምእንኳን ጥቃቱ የሞት አደጋ ያላደረሰ ቢሆንም በሁለቱ የረጅም ጊዜ ባላንጣዎች መካከል ይፋዊ ጦርነት ይቀሰቀሳል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ላይ እስራኤል የኢራንን ጥቃት እንድታከሽፍ የረዳቻት አሜሪካ እስራኤል በምትወስደው መልሶ ማጥቃት ላይ አትሳተፍም ሲሉ ለኔታንያሁ ነገረዋቸዋል።
በጋዛ ጦርነት ከተጀመረ ከባለፈው ጥቅምት ወር ወዲህ እስራኤል በኢራን ይደገፉሉ ከሚባሉት በሊባኖስ፣ በሶሪያ፣ በየመን እና በኢራቅ ካሉ ታጣቂዎች ጋር ግጭት ውስጥ ገብታለች።
እስራኤል በኢራን ላይ የአጸፋ ምላሽ ከመስጠት እንድትቆጠብ አለምአቀፍ ጫና በርትቶባታል።
የአውሮፖ ህብረት የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል "ገደል አፋፍ ላይ ነው ያለነው" ስሆነም "የኋላ ማርሽ ረግጠን መመለስ አለብን" ብለዋል።
የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ የጀርመን መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ፣ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን ተመሳሳይ መልእክት አስተላልፈዋል። አሜሪካ እና የተመድ ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝም እስራኤል ምላሽ ከመስጠት እንድትቆጠብ ጥሪ አቅርበዋል።
አጋሯን ኢራንን በይፋ ከመተቸት የተቆጠበችው ሩሲያም ሁለቱም ወገኖች ግጭት ከማባባስ እንዲቆጠቡ አሳስባለች።
"ግጭት በማባባስ ማንም ተጠቃሚ አይሆንም" ብለዋል የክሬሚሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ።
ቻይና፣ ኢራን ጉዳዩን በብልሃት እንደምትይዘው እና ተጨማሪ ቀጣናዊ ቀውስ እንዳይፈጠር እንደምታደርግ ያላትን እምነት ገልጻለች።