የኢራን ጦር እስራኤል የምትስነዝረውን ማንኛውንም ጥቃት እንደአመጣጡ ለመመከት ዝግጁ መሆኑን ገለጸ
የእስራኤል ጦር አዛዥ በትናንትናው እለት እስራኤል ኢራን ላደረሰችው ጥቃት ምላሽ እንደምትሰጥ ተናግረዋል
የኢራኑ ፕሬዝደንት ኢብራሂም ራይሲ "በጽዮናዊው መንግስት በመሬታችን ላይ የሚፈጸም ማንኛውም ጥቃት ከባድ ምላሽ ይሰጠዋል" ሲሉ ተናግረዋል
ኢራን በዛሬው እለት እንደገለጸችው ጦሯ ከእስራኤል በኩል ሊሰነዘር የሚችልን ማንኛውንም አይነት ጥቃት ለመመከት ዝግጁ ነው።
የኢራን አየር ኃይል እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችለውን ልምምድ እያደረገ እንደሚገኝ የገለጸ ሲሆን የኢራን የባህር ኃይል ደግሞ በቀይ ባህር የሚንቀሳቀሱ የኢራን መርከቦችን እጀባ እያደረገ ነው ብለዋል።
ኢራን በሶሪያ ደማስቆ በሚገኘው ኢምባሲዋ ላይ ጥቃት በማድረስ እና ሁለት ጀነራሎችን ጨምሮ ሰባት ሰዎችን በመግደል በከሰሰቻት እስራኤል ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀጥተኛ ጥቃት ባለፈው ሳምንት አድርሳለች።
የሀገሪቱን የ'ጦር ቀን' ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው ወታራዊ ትርኢት ላይ የተገኙት የኢራኑ ፕሬዝደንት ኢብራሂም ራይሲ "በጽዮናዊው መንግስት በመሬታችን ላይ የሚፈጸም ማንኛውም ጥቃት ከባድ ምላሽ ይሰጠዋል" ሲሉ ተናግረዋል።
በትርኢቱ ድሮኖቿን፣ሚሳይሎቿን እና ወታደሮቿን ያሳየችው ኢራን፣ ባለፈው ሳምንት ያደረሰችውን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል ለምትሰጠው ምላሽ ዝግጁ መሆኗን የሚገልጽ መልእክት አስተላልፋለች።
በዚሁ ፕሮግራም ላይ የተገኙት የኢራን አየር ኃይል አዛዥ ሩሲያ ሰራሽ ሱ-24 የጦር ጀቶችን ጨምሮ ሁሉም የጦር አውሮፕላኖች እስራኤል ልትቃጣው የምትችለውን ጥቃት ለመመከት ዝግጁ ናቸው ብለዋል።
"የኢራንን የአየር ክልል መሸፈንን እና መዋጋትን ጨምሮ በሁሉም ዘርፍ ዝግጁ ነን" ሲሉ አዛዡ ብርጋዴር ጀነራል አሚር ቫሄዲ ተናግረዋል።
በኢራን ከተወነጨፉት 300 ሚሳይሎች እና ድሮች አብዛኞቹን ማክሸፏን እና በሰው ህይወት ላይ ጉዳት አለመድረሱን የገለጸችው እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት እንደምትሰነዝር በትናንትናው እለት አስታውቃለች።
የእስራኤል ጦር አዛዥ ሄርዚ ሀለቪ እስራኤል ምላሽ ትሰጣለች ብለዋል።
"ወደ እስራኤል ግዛት በርካታ ሚሳይሎችን እና ድኖሮችን የማስወንጨፍ ተግባር ምላሽ ያስፈልገዋል።"
እስራኤል በአጸፋ በኢራን ሪቮሉሽናሪ ጋርድ ካምፖች ወይም በኑክሌር የምርምር ጣቢያዎች ላይ ጥቃት ልታደርስ ትችላለች የሚል ስጋት ተፈጥሯል።
የአውሮፓ ህብረት፣ ተመድ እና አሜሪካ፤ እስራኤል በኢራን ላይ እርምጃ ከመውሰድ እንድትታቀብ ጫና እያሳደሩበት ነው።