የመንግስታቱ ድርጅት በሱዳን ከ100 በላይ ሰዎች የተገደሉበትን ጥቃት አወገዘ
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይል (አርኤስኤፍ) በጀዚራህ ግዛት በከባድ መሳሪያዎች ጥቃት ከፍቶ 104 ንጹሃን መገደላቸውን የመብት ተሟጋቾች ገልጸዋል
ፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ በበኩሉ በሱዳን ጦር ጋር ካምፖች ላይ እንጂ በንጹሃን ላይ ጥቃት አለመፈጸሙን አስታውቋል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሱዳን ከ100 በላይ ሰዎች የተገደሉበትን ጥቃት አወገዘ።
የድርጅቱ ዋና ጸሃፊ በጀዚራህ ግዛት ዋድ አል ኑራ በተባለው አካባቢ በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይል (አርኤስኤፍ) ተፈጽሟል የተባለውን ጥቃት አጥብቀው መቃወማቸውን ቃልአቀባያቸው ስፌፋን ዱጃሬክ ተናግረዋል።
በሱዳን እየተፋለሙ የሚገኙት ሃይሎች ንጹሃንን ኢላማ ካደረገ ጥቃት እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።
በጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) የሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ሃይል ከትናንት በስቲያ በዋድ አል ኑራ በከባድ መሳሪያዎች ጭምር በፈጸመው ጥቃት 104 ንጹሃን መገደላቸውን “መዲና ሬዚስታንስ ኮሚቴ” የተባለው የመብት ተሟጋች ገልጿል።
የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ካትሪና ሩሴል ባወጡት መግለጫም በጥቃቱ ህይወታቸው ካለፈው ውስጥ 35ቱ ህጻናት መሆናቸውን መግለጻቸውን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይል በበኩሉ የቀረበበትን ክስ ውድቅ አድርጓል።
የሱዳን ጦር በጀበል አል አውሊያ ጥቃት ሊከፍትብን ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ስንረዳ በዋድ አል ኑራ በሚገኙ ሶስት ካምፖቹ ላይ ጥቃት ፈጽመናል እንጂ ንጹሃን ላይ ያነጣጠረ ጥቃት አላደረስንም ሲልም በኤክስ (ትዊተር) ገጹ ላይ አስፍሯል።
የዋድ አል ኑራ ነዋሪዎች የተገደሉት በሁለቱ ተፋላሚዎች መካከል በተደረጉ የተኩስ ልውውጦች መሆኑንም ነው ያብራራው።
በሱዳን የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ ድጋፍ አስተባባዋ ክሌመንታይን ንዌታ ሳላሚ በበኩላቸው ተፋላሚዎቹ አካላት ህዝብ በሚኖርባቸው ከተሞችና መንደሮች በከባድ መሳሪያዎች መዋጋታቸው የንጹሃንን ህይወት መቅጠፉን ተናግረዋል።
በዋድ አል ኑራ የተፈጸመው ጥቃት በገለልተኛ አካል ተጣርቶ ተጠያቂነት እንዲሰፍንም ጥሪ አቅርበዋል።
ኦማር ሀሰን አልበሽርን ከስልጣን ለማንሳት የተባበሩት ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን እና ጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ ባለፈው አመት ሚያዚያ ወር የጀመሩት ጦርነት ከ14 ሺህ በላይ ሱዳናውያንን ህይወት ቀጥፏል።
ጦርነቱ በሀገር ውስጥ የተፈናቀሉና ወደ ጎረቤት ሀገራት የተሰደዱ ሱዳናውያንን ቁጥር 9 ሚሊየን በማድረስ ምስራቅ አፍሪካዊቷን ሀገር በተፈናቃይ ብዛት ከአለም ቀዳሚዋ አድርጓታል።
ሳኡዲ አረቢያ፣ የኢጋድ መቀመጫዋ ጂቡቲ እና ኬንያ ተፋላሚዎቹን ጀነራሎች ፊት ለፊት ለማደራደር ያደርጓቸው ጥረቶችም ሳይሳኩ ቀርተው ፍልሚያቸው የሱዳናውያንን ሰቆቃ ማባባሱን ቀጥሏል።