“ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ህግጋት ሊከበሩ ይገባል”- የአውሮፓ ህብረት
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከአውሮፓ ህብረት ምክትል ፕሬዚዳንት ጋር በብራሰልስ መክረዋል
“በመሰረታዊነት አጀንዳው የሃገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ነው”- ደመቀ መኮንን
“በመሰረታዊነት አጀንዳው የሃገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ነው”- ደመቀ መኮንን
አውሮፓ የሚገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከአውሮፓ ህብረት ምክትል ፕሬዚዳንት ጆሴፕ ቦሬል ጋር በብራሰልስ ተወያዩ።
አቶ ደመቀ በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ የህብረቱ የውጭ እና የደህንነት ጉዳይ ተወካይ ለሆኑት ጆሴፕ ቦሬል አብራርተዋል።
ጆሴፕ በበኩላቸው ከብሄር ተኮር ጥቃቶች ከሰብዓዊ መብት እና የህግ ጥሰቶች ጋር በተያያዘ ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል፡፡
“ግጭቱ ቀጣናውን ሊያተራምስ የሚችል ነው የሚል ትንታኔዬን ቀድሞውኑ አስቀምጬ ነበር” ነው ቦሬል በመግለጫቸው ያሉት፡፡
የማይካድራው ጭፍጨፋ ብቻ የቡድኑን የክፋት ጥግ የሚያሳይ ነው ያሉት አቶ ደመቀም “የህወሓት ቡድን በየጊዜው የሚፈፀማቸው ዘግናኝ ጥፋቶች ሃገሪቷን እና ቀጣናውን ወደለየለት ትርምስ የሚያስገባ” እንደነበር ስለማስታወሳቸው ከጽህፈት ቤታቸው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የሃገር እና የህዝብን ህልውና ለማስጠበቅ በመንግስት እየተወሰደ ያለው ህግ የማስከበር እርምጃ “ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል” ሲሉም ነው አቶ ደመቀ የገለጹት።
በኢትዮጵያና በቀጣናው በዋናነትም በሱዳን ስላለው “የተበላሸ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ” መክረናል ያሉት ቦሬል“ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ህግጋት ሊከበሩ” እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ህብረቱ ውይይቱን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
“የሰላማዊ ዜጎች፣ተፈናቃዮች እና ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች እንቅስቃሴ እንዳይገታ እና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ”በህብረቱ ስም ጥሪ ማቅረባቸውንም ነው ምክትል ፕሬዝዳንቱ የተናገሩት፡፡
ህብረቱ “ግልጽ ነው”በሚል ያስቀመጠውን መልዕክት “ለተጋለጡ ዜጎች ሁኔታዎች እንዲመቻቹ፣ ግጭቱ እንዲቆም፣ ጣልቃ ገብነት እንዳይኖር እና የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት እንዲጠበቅ”ሲል አስተላልፏል፡፡
በአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ከተላከው ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ጋር በመተባበር የውይይት በርን መክፈት ተጨማሪ ትርምሶችን እንደሚያስቀርም ነው ያስቀመጠው፡፡
ሰብዓዊ ድጋፎችን ለተመለከቱ ስጋቶች ምላሽ የሰጡት አቶ ደመቀ “ጥንቃቄ እና ሃላፊነት በተሞላበት አግባብ አስፈላጊው ሁሉ”እንደሚከናወን አስረድተዋል።
በመሰረታዊነት “አጀንዳው የሃገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ነው” ብለዋል አቶ ደመቀ፡፡
መንግስትያለማንም ጣልቃ ገብነት በሉዓላዊነት ላይ በተጋረጠው ፈተና ላይ የጀመረውን ህግን የማስከበር እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ለምክትል ፕሬዝዳንቱ ያረጋገጡት።