የአውሮፓ ህብረት ዩክሬናውያን “ለኡላዊነታቸው በሚያደርጉት ትግል ከጎናቸው” እንሚቆም ገለጸ
ጆሴፕ ቦሬል፤ “ዩክሬናውያን ላለፉት ስድስት ወራት በጀግንነት እየተዋደቁ ነው” ብለዋል
የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ተወካዩ “ነፃነት ማለት ለዩክሬናውያን ከምንም በላይ ነው” ሲሉም ተናግረዋል
ዩክሬናውያን ለነጻነታቸውና ልኡላዊነታቸው በሚያደርጉት ትግል ከጎናቸው መቆሙ እንደሚቀጥልበት የአውሮፓ ህብረት ምክትል ፕሬዝዳንትና የውጭ ጉዳይ እና የደህንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይ ጆሴፕ ቦሬል ገለጹ፡፡
ጆሴፕ ቦሬል የዩክሬን 31ኛ የነጻነት በዓል ምክንያት በማድረግ በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ ፤ አውሮፓ ህብረት አሁንም ከዩክሬን ጎን ነው ብለዋል፡፡
“ሩሲያ ዓለም አቀፍ ህጎችንና ቃል ኪዳኖችን በመጣስ በዩክሬን ላይ የጀመረችው ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት ለመመከትና የራሳቸውን የወዲፊት እድል ለመወሰን፤ ዩክሬናውያን ላለፉት ስድስት ወራት በጀግንነት እየተዋደቁ ነው” ያሉት ቦሬል፤ የአውሮፓ ህብረት ለዩክሬናውያን ትግል ትልቅ ክብር እንዳለውም ተናግረዋል፡፡
“ነፃነት ማለት ለዩክሬናውያን ከምንም በላይ ነው”ም ያሉት ቦሬል፡፡
እንደ ቦሬል ሁሉ የአውሮፓ ህብረት የወቅቱ ፕሬዝዳንት የፈረንሳዩ ኢማኑኤል ማክሮን በትናንትነው እለት ባስተላለፉት መልእክት ህብረቱ ዩክሬንን “ለረዥም ጊዜ” ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
ማክሮን ዛሬ በኪቭ ውስጥ በክሬሚያ ፕላትፎርም ኮንፈረንስ ላይ ለተሳተፉ ተሳታፊዎች ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት፤ ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ከስድስት ወራት በኋላም ቢሆን ዩክሬንን ለመደገፍ ያለን "ቁርጠኝነታችን አልተቀየረም እንዲሁም ይህን ጥረት ለረጅም ጊዜ ለማቆየት ዝግጁ ነን" ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
በዩክሬን ለተፈጠረው መጠነ ሰፊ ቀውስ ሩሲያን ተዋቃሽ ያደረጉት ማክሮን፤ የዩክሬን ጉዳይ ሁሉም በዓለም ላይ የሚኖር ሰው የነጻነት ጉዳይ መሆኑም ተናግረዋል፡፡
አውሮፓ ህብረት የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት ተከትሎ ለዩክሬን ከሚያደርገው የጦር መሳሪያ በዘለለ ሞስኮ ላይ እስከ 2023 ጸንተው የሚቆዩ በርካታ ማዕቀቦች እንደጣለ የሚታወቅ ነው፡፡