አውሮፓ ህብረት ዩክሬንን ለረዥም ጊዜ ለመደገፍ ዝግጁ ነው- ኢማኑኤል ማክሮን
ማክሮን፤ አሁን ያለው ዓለም አቀፍ ቀውስ ሞስኮ በየካቲት 24 በዩክሬንን ላይ የወሰደችውን ምርጫ ተከትሎ የመጣ ነው ብለዋል
ኢማኑኤል ማክሮን የውቅቱ የአውሮፓ ህብረት ፕሬዝዳንት ናቸው
አውሮፓ ህብረት ዩክሬንን “ለረዥም ጊዜ” ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑ የውቅቱ የህብረቱና የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ተናገሩ፡፡
ማክሮን ዛሬ በኪቭ ውስጥ በክሬሚያ ፕላትፎርም ኮንፈረንስ ላይ ለተሳተፉ ተሳታፊዎች ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት፤ ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ከስድስት ወራት በኋላም ቢሆን ዩክሬንን ለመደገፍ ያለን "ቁርጠኝነታችን አልተቀየረም እንዲሁም ይህን ጥረት ለረጅም ጊዜ ለማቆየት ዝግጁ ነን" ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
"ይህ የዓለም አቀፉ ደረጃ የተስተዋለው አለመረጋጋት እንዲሁም ከኃይልና የምግብ አቅርቦት ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ሰብዓዊ ቀውስና የተከሰተው መስተጓጎል ፤ ሩሲያ በየካቲት 24 ዩክሬንን ለማጥቃት የወሰደችውን ምርጫ ተከትሎ የመጣ ውጤት ነው" ማለታቸውም ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
“በዚህ ላይ ምንም ዓይነት ድክመት፣ የመስማማት መንፈስ ሊኖር አይችልም፣ ምክንያቱም ይህ ሁሉም በዓለም ላይ የሚኖር ሰው የነጻነትና ጉዳይ ነው” ሲሉም አክለዋል ማክሮን።
ኢማኑኤል ማክሮን ከአንድ ወር በፊት የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነትን በተመለከተ ለጋዜጦች በሰጡት ቃለ ምልልስ፤ ፑቲን በዩክሬን ጉዳይ “ታሪካዊ ስህተት ሰርቷል“ ማለታቸው አይዘነጋም፡፡
"እኔ እንደማስበው እና እንደነገርኩት ፑቲን ለህዝቡ፣ለታሪክ እንዲሁም ለራሱ ታሪካዊ እና መሰረታዊ ስህተት እየሰራ ነው" ያሉት ማክሮን፤ ዲፕሎማሲያዊ መውጫ መንገድን ማፈላለግ እንጂ “ሩሲያን ማዋረድ የለብንም” ሲሉም ነበር ያሳሰቡት።
ፈረንሳይ አስታራቂ ሚና እንደሚኖራት እርግጠኛ ነኝም ብለዋል በወቅቱ፡፡
ሞስኮ በየካቲት ወር በዩክሬንን ላይ ልዩ ነው ያለችውን ወታደራዊ ዘመቻ መጀመሯን ተከትሎ፤ ማክሮን ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር መወያየታቸው የሚታወቅ ነው።
ይሁን እንጂ ማክሮን የተጓዙበት መንገድ ውጥረቱን ከማርገብ ይልቅ ጥረቶችን የሚጎዳ ነው በሚል መተቸታቸው ይታወሳል፡፡
አውሮፓም ሆነ ምዕራባውያን የዩክሬን አጋሮች፤ የሩሲያ ወታደራዊ የበላይነትን ለመግታት ያስቻሉ በቢሊዮን ዶላሮች የመገመቱ የጦር መሳሪያዎች ቢያቀርቡም፤ የዩክሬን ምስራቅ እና ደቡብ ሰፋፊ ክፍሎችን ከያዙት የሩሲያ ኃይሎች ጋር የሚደረገውን ውጊያ አሁንም ድረስ እንደቀጠለ ነው፡፡