በእለቱ ለጦርነቱ ሰለባዎች የህሊና ጸሎት ተደርጓል
በጦርነት ውስጥ የምትገኘው ዩክሬን የሠንደቅ ዓላማ ቀንን አከበረች።
የሰንደቅ ዓላማ ቀኑ የሃገሪቱን ብሔራዊ የነጻነት ቀን ታሳቢ አድርጎ የሚከበር ሲሆን በአከባበር ስነ ስርዓቱ ላይ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ተገኝተዋል።
በዓሉን አስመልክተው ባደረጉት ንግግር፤ ሰማያዊ እና ቢጫው የዩክሬን ሰንደቅ ክሬሚያን ጨምሮ በሩሲያ በተያዙ ሌሎችም የሃገሪቱ ግዛቶች መውለብለቡ እንደማይቀር ተናግረዋል።
ዩክሬን ብሔራዊ የነጻነት ቀን አድርጋ የምታከብረው ከቀድሞዋ ታላቋ ሶቪየት ህብረት አገዛዝ 'ነጻ ወጣሁ' የምትልበትን በጎርጎሮሳዊያኑ ነሐሴ 24ን (1991)ን ነው።
የሰንደቅ ዓላማ ቀኑ ደግሞ በዋዜማው ነሐሴ 23 በየዓመቱ ይከበራል።
ቀኑ የሶሻሊስት ሶቪዬት ህብረት የተወካዮች ምክር ቤት አባል የነበሩ ዩክሬናውያን ሰማያዊ እና ቢጫ ቀለም ያለው ባንዲራ ይዘው ወደ ፓርላማው የገቡበትን ቀን ታሳቢ በማድረግ የሚከበር ነው።
አባላቱ በወቅቱ ፓርላማው የዩክሬንን ነጻ ሃገርነት እንዲቀበል እና ሰማያዊ እና ቢጫ ቀለም ያለው ባንዲራዋ ደግሞ መለያ ሰንደቅ ዓላማዋ እንዲሆን ጠይቀው ነበር።
ጥያቄውን የተቀበለው ፓርላማውም በማግስቱ ነሐሴ 24 ቀን 1991 ዩክሬን ነጻ እና ሉዓላዊ ሃገር መሆኗን አውጇል።
በዚህም ነሐሴ 24 የነጻነት ቀን፤ ዋዜማው ነሐሴ 23 ደግሞ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ሆኖ በዩክሬናውያን ዘንድ በየዓመቱ ይከበራል። የትናንቱ የሰንደቅ ዓላማ ቀንም ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ የተከበረ ነው።
ሩሲያ 'ልዩ' ያለችውን ዘመቻ በዩክሬን ማካሄድ ከጀመረች 6 ወራት ተቆጥረዋል። በነዚህ ወራትም የሃገሪቱን ዋና ከተማ ኪቭን ተቆጣጥራ በምዕራባውያን ይደገፋል የምትለውን የዜሌንስኪን መንግስት ለመቀየር ባትችልም በስተምስራቅ ባደረገችው የተሳካ ዘመቻ ሰፊ የሃገሪቱን ክፍል መቆጣጠር ችላለች፡፡
ያን ተከትሎም ነው፤ ወትሮም ቢሆን 'ልባቸው ከሩሲያ ጋር ነው' ለሚባልላቸው፤ የዶኔስክ እና ሉሃንስክ ግዛቶች ከዩክሬን ተገንጥለው ሃገር የሚሆኑበትን የህዝባዊ ሪፐብሊክነትን እውቅና በይፋ የሰጠችው።
እውቅናውን መደገፏን ቀድማ ያስታወቀችው ሶሪያም ከሁለቱ ህዝባዊ ሪፐብሊኮች ጋር በቅርቡ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን እንደምትጀምር አስታውቃለች።