የአውሮፓ ህብረት ከሩሲያ ጋር ያለውን “የቪዛ ማመቻቸት ስምምነት” ሊያቆም ይችላል ተባለ
የተወሰኑ የህብረቱ አባል ሀገራት የሩስያ የቱሪስት ቪዛ ሙሉ በሙሉ እንዲታገድ እስከመጠየቅ ደርሰዋል
ጆሴፕ ቦሬል፤ ሁሉም ሩሲያውያን ወደ አውሮፓ እንዳይገቡ መከልከል "ጥሩ ሀሳብ አይደለም" ብለዋል
የአውሮፓ ህብረት ከሩሲያ ጋር ያለውን የቪዛ ማመቻቸት ስምምነት ሊያቆም ይችላል ተባለ።
ለዚህም የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ህብረቱ ከሞስኮ ጋር ያለውን የቪዛ ስምምነት ለማቆም ከሚያስችል ውሳኔ ለመድረስ መዘጋጀታቸው ኤኤፍፒ የዲፕላመቲክ ምንጮቹን መረጃ ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።
የህብረቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሩሲያ ዜጎችን የጉዞ ፈቃድን ለመገደብ በሚያስችላቸው ጉዳይ ላይ መወያየታቸውንም ነው የተገለጸው።
አንዳንድ አባል ሀገራት የሩስያ የቱሪስት ቪዛ ሙሉ በሙሉ እንዲታገድ እስከመጠየቅ ቢደርሱም፤ ኃሳቡ በብዙዎቹ ተቀባይነት ሳያገኘ ቀርቷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ የቪዛ ስምምነቱን ለማቋረጥ የሚያስችላቸው የመጀመሪያ እርምጃ ለመውሰድ በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት (ማክሰኛ እና እሮብ) በቼክ ሪፓብሊኳ መዲና ፕራግ በሚኖረው ህብረቱ ስብሰባ እቅዳቸው ፖለቲካዊ ድጋፍ እንዲኖረው ለማድረግ እንደሚሰሩም ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአውሮፓ ህብረት የውጭ ፖሊሲ ኃላፊ ጆሴፕ ቦሬል ፤ ወደ አውሮፓ ህብረት የሚገቡ የሩሲያ ተጓዦች ላይ ሙሉ በሙሉ እገዳን ተግባራዊ ለማድረግ የቀረበውን ሀሳብ ውድቅ አድርገውታል።
ቦሬል ሁሉም ሩሲያውያን ወደ አውሮፓ ህብረት እንዳይገቡ መከልከል "ጥሩ ሀሳብ አይደለም"ም ብለዋል።
ያም ሆኖ ፤እንደ ኢስቶኒያ እና ፊንላንድ ያሉ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት በሩሲያ ቱሪስቶች ላይ ቪዛን ለመገደብ የሚያስችሉ እርምጃዎች ቀደም ሲል መውሰድ መጀመራቸው የሚታወቅ ነው።