የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት “የአውሮፓ ሀገራት ለሩሲያ ሃብታሞች ቪዛ ሊከለክሉ ይገባል” አሉ
ዜለንስኪ ለሩሲያውያን የቪዛ ክልከላ ጥያቄ ቢያቅርቡም በአውሮፓ ህብረት በኩል እስካሁን የተባለ ነገር የለም
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ፣ “ሩሲያውያንን የማግለል ሙከራ ምንም ተስፋ የሌለው ሂደት ነው” ብለዋል
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት “አውሮፓን የሩሲያ ሃብታሞች ሱፐርማርኬት” ላለማድረግ ለሩሲያ ዜጎች ቪዛ ሊከለክሉ ይገባል ሲሉ ጥሪ አቀረቡ።
ዘሌንስኪ፤ የቪዛ ክልከላ ሃሳቡ የሩሲያ ሀብታሞችን እንጅ የቭላድሚር ፑቲን ፖሊሲን በመቃወም ነጻነታቸውን እና ህይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው እርዳታ የሚፈልጉ ሩሲያውያን አይመለከተም ብለዋል።
የሩሲያ ገዳዮች ወይም የመንግስት ሽብር ተባባሪዎች የሼንገን ቪዛ እንዳይጠቀሙ የሚያደረግ ዋስትና ሊኖር ይገባልም ነው ያሉት ዘሌንስኪ።
ዘሌንስኪ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ከዋሽንግተን ፖስት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የቪዛ እገዳን በተመለከተ ማንሳታቸውና “ሩሲያውያን ፍልስፍናቸውን እስኪቀይሩ ድረስ በራሳቸው ዓለም ውስጥ መኖር አለባቸው” ሲሉ መደመጣቸው አይዘነጋም።
ዜለንስኪ ይህን ይበሉ እንጅ በአውሮፓ ህብረት በኩል እስካሁን የተባለ ነገር እንደሌለ ሮይተርስ ዘግቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ የዜለንስኪን ሃሳብ አውግዘዋል።
“ሩሲያውያንን ወይም ሩሲያን ለማግለል የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ ምንም ተስፋ የሌለው ሂደት ነው” ብለዋል ቃል አቀባዩ።