የሩሲያው ጋዝፕሮም በኖርድ ስትሪም 1 ወደ አውሮፓ የሚገባውን ጋዝ በ20 በመቶ ቀነሰ
ኖርድ ስትሪም የጋዝ መስተላለፊያ መስመር የተዘጋው በጥገና ምክንያት እንደሆነ ጋዝፕሮም አስታውቋል
ጋዝፕሮም ወደ አውሮፓ የሚልከውን የጋዝ መጠን በ33 ሚሊየን ኪዩቢክ ሜትር እንደሚቀንስ አሳውቋል
የሩሲያው ግዙፍ የኃይል አቅራቢ ድርጅት “ጋዝፕሮም” በኖርድ ስትሪም አንድ በኩል ወደ አውሮፓ የሚገባውን የተፈጥሮ ጋዝ መጠን ከዛሬ ጀምሮ በ20 በመቶ መቀነሱ ተገለፀ።
ጋዝፕሮም ቀደም ብሎ ከትናንት 10 ሰዓት ጀምሮ በግዙፉ የጋዝ ማስተላፊያ በኩል ወደ አውሮፓ የሚገባው የጋዝ መጠን በ33 ሚሊየን ኪዩቢክ ሜትር እንደሚቀንስ አሳውቆ ነበር።
- “ያለ ሩሲያ ጋዝና ነዳጅ እንዴት መቀጠል ይቻላል” የሚለው የአውሮፓ ሀገራትን ማሳሰቡ ተገለፀ
- የሩስያ ጋዝ ላይ የሚጣሉ እገዳዎች መካከለኛው አውሮፓ ኢኮኖሚን ክፉኛ እንደሚጎዳ ተገለፀ
የሩስያ ኩባንያ እርምጃውን የወሰደው የሀገሪቱ የፌደራል ቴክኒካል ክትትል ኤጀንሲ ከሮስቴክናድዞር በተሰጠው ትእዛዝ መሰረት መሆኑን አስታውቋል።
በዚህም በኖርድ ስትሪም አንድ በኩል የሚተላለፈው የጋዝ መጠን በ20 በመቶ እንዲቀንስ የተደረገው፤ በፖርቶቫያ ቤይ በሚገኘው የመጭመቂያ ጣቢያ በሚገኝ የተርባይን ሞተር ጥገና ስለሚያስፈልገው ነው ብሏል።
ባሳለፈው ሳምንት ኖርድ ስትሪም አንድ ከ10 ቀናት የጥገና ሥራ በኋላ አቅርቦቶችን እንደገና መጀመሩ የሚታወስ ሲሆን፤ ነገር ግን እያቀረበ ያለው የነዳጅ መጠን ካለው አቅም በ 40 በመቶ ብቻ ነው።
ሩሲያ ወደ አውሮፓ ሀገራ የምታደርሰው ጋዝን መቀነሷ በአውሮፓ ሀገራት ውስጥ ከፍተኛ ስጋትን የፈጠረ ሲሆን፤ በአውሮፓ ከአቅርቦት እጥረት ስጋት ጋር በተያያዘ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ እያሳየ ነው
በትናትናው እለት ብቻ የአንድ በርሜል የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በ1.2 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፣ ጭማሪውም ለተከታታይ ሁለተኛ ቀን የተመዘገበ ነው።
አሁን ላይ አንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ በ106 የአሜሪካ ዶላር እየተሸጠ መሆኑንም የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል።
የዋጋ ጭማሪው የተከሰተው ሩሲያ ወደ አውሮፓ የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ የሆነውን ኖርድ ስትሪምን ለጥገና በሚል ልትዘጋው እንደሆነ ዜና መውጣቱን ተከትሎ ነው።