የአውሮፓ ህብረት መሪዎች ለዩክሬን የ54 ቢሊየን ዶላር ለመስጠት ተስማሙ
የሀንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን ያሰሙት ተቃውሞ ድጋፉ እንዳይጸድቅ ምክንያት ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል
የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት በዚህ ወር መጨረሻ ሁለተኛ አመቱን ይይዛል
የአውሮፓ ህብረት መሪዎች ለዩክሬን የ54 ቢሊየን ዶላር ለመስጠት ተስማሙ።
መሪዎቹ ዛሬ በብራሰልስ ባካሄዱት ምክክር ነው ለኬቭ ድጋፍ እንዲደረግ መስማማታቸው የተነገረው።
የአውሮፓ ህብረት ምክርቤት ፕሬዝዳንት ቻርለስ ሚሸል 27ቱም የህብረቱ አባል ሀገራት ከህብረቱ በጀት ላይ ለዩክሬን 54 ቢሊየን ዶላር እንዲሰጣት መስማማታቸውን በኤክስ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
የሀንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን በታህሳስ ወር ህብረቱ ለዩክሬን ለማድረግ ያሰበውን ድጋፍ መቃወማቸው ይታወሳል።
ባለፉት ሳምንታትም ሌሎች የህብረቱ መሪዎች ቪክቶር ኦርባንን ለማሳመን ጥረት ማድረጋቸውን ነው ሬውተርስ ያስታወሰው።
በዛሬው የብራሰልስ ስብሰባ የታደሙት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ወዳጁ ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን ለኬቭ ይደረጋል ስለተባለው ድጋፍ አስተያየት አልሰጡም።
ከጋዜጠኞች በጉዳዩ ዙሪያ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበውም በማህበራዊ ትስስር ገጾቻቸው የአውሮፓ ገበሬዎች በብራሰልስ የሚያካሂዱትን የተቃውሞ ሰልፍ ምስሎች አጋርተዋል።
የአውሮፓ ህብረት ለዩክሬን ያጸደቀው ግዙፍ የፋይናንስ ድጋፍ እስከ 2027 የሚለቀቅ ነው ተብሏል።
የምዕራባውያንን ድጋፍ አጥብቃ የምትፈልገው ኬቭ በቅርቡም ከሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ ማግኘቷ ይታወሳል።
አሜሪካም ለዩክሬንና እስራኤል ለመስጠት ያሰበችው የ110 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ በቅርቡ ስምምነት ላይ እንደሚደረስበት ነው የሚጠበቀው።
ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ በአውሮፓ ምድር የተከሰተውና በዚህ ወር መጨረሻ ሁለተኛ አመቱን የሚይዘው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት የመቶ ሺዎችን ህይወት ቀጥፎ ቢሊየን ዶላሮችን እያወደመም የሚያስቆመው አለማቀፍ ሃይል አልተገኘም።
ክሬምሊንም የምዕራባውያኑ የወታደራዊ ድጋፍ እየጨመረ መሄድ የኒዩክሌር ጦርነት ሊያስጀምረን ይችላል የሚለውን ማስጠንቀቂያዋን ማሰማቷን ቀጥላለች።