ሩሲያ ራሷን ለኑክሌር ጦርነት እያዘጋጀች እንደሆነ ተገለጸ
የሩሲያ ወታደራዊ አካዳሚ በምድር ውጊያ ላይ የኑክሌር አረር አጠቃቀም ልምምድ ማድረጊያ ይፋ አድርጓል
ልምምዱ በአቶሚክ ቦምብ እና ሌሎች ከባድ አውዳሚ የጦር መሳሪያዎችን ማድረግ ያካተተ ነው ተብሏል
ሩሲያ ራሷን ለኑክሌር ጦርነት እያዘጋጀች እንደሆነ ተገለጸ።
የዓለማችን ቀዳሚ የኑክሌር አረር ባለቤት የሆነችው ሩሲያ በምድር ላይ እጅግ አውዳሚ የሚባሉ ጦርነቶችን ማድረግ የሚያስችል ማሰልጠኛ መሳሪያ መፈብረኳ ተገልጿል።
ታስ የተሰኘው የሩሲያ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው ሩሲያ በምድር ላይ አውዳሚ የሚባሉ የአቶሚክ ቦምብ እና በኑክሌር ጦር የታገዙ ጦርነቶችን ማካሄድ እና መመከት የሚያስችል ወታደራዊ ልምምዶችን ለማድረግ አቅዳለች።
ለዚህ ልምምድ እንዲረዳትም ለወታደሮቿ ስልጠናውን መስጠት የሚያስችላትን መለማመጃ በሀገሪቱ ጦር አካዳሚ ተመራማሪዎች መሰራቱም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
ከዚህ በተጨማሪም የጦር ልምምዱ የኬሚካል ፣ጨረር እና ባዮሎጅካል የጦር መሳሪያዎች የታገዙ ጦርነቶችን ማካሄድ የሚያስችሉም ናቸው ተብሏል።
የሩሲያ የጸጥታ እና ወታደራዊ መሪዎች ከዚህ በፊት እንዳሉት ዩክሬን በምዕራባዊያን ሀገራት ድጋፍ በምታገኛቸው የረጅም ርቀት ጦር መሳሪያዎች ታግዛ ወደ ግዛቷ ዘልቃ ጥቃት ካደረሰች ሞስኮ ራሷን ለመጠበቅ የኑክሌር ጦር መሳሪያዎቿን ልትጠቀም ትችላለች ሲሉ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።
ሩሲያ እና አሜሪካ በዓለም ላይ ካሉ የኑክሌር ጦር ሙሳሪያዎች ውስጥ 98 በመቶ ያህሉን የያዙ ሀገራት ናቸው።