የተመድ ፍርድ ቤት ዩክሬን በሩሲያ ላይ ካቀረበቻቸው ክሶች መካከል አብዛኞቹን ውድቅ አደረገ
ውድቅ ከተደረጉት የዩክሬን ክሶች መካከል ሩሲያ ካሳ ትክፈለኝ የሚለው አንዱ ነበር
16 ዳኞች የተሳተፉበት የሄጉ ፍርድ ቤት ሩሲያ ሁለት የተመድ ስምምነት ህጎችን ጥሳለች ተብሏል
የተመድ ፍርድ ቤት ዩክሬን በሩሲያ ላይ ካቀረበቻቸው ክሶች መካከል አብዛኞቹን ውድቅ አደረገ።
ላለፉት ሁለት ዓመታት ጦርነት ውስጥ ያሉት ሩሲያ እና ዩክሬን ከጦር ሜዳ ባለፈ በተመድ ስር በተቋቋመው የሄግ ዓለም አቀፍ ችሎት ላይ እየተከራከሩ ናቸው።
ዩክሬን ዋና መቀመጫውን ስዊዘርላንድ ሄግ ላይ ላደረገው ዓለም አቀፉ የግልግል ፍርድ ቤት በርካታ ክሶችን በሩሲያ ላይ መስርታ ነበር።
16 ዳኞች የተሳተፉበት ይህ የግልግል ችሎት አብዛኞቹን የዩክሬን ክሶችን ውድቅ ሲያደርግ ሁለት ክሶችን ደግሞ ሩሲያ ጥፋተኛ ነች ብሏል።
ዩክሬን ከመሰረተቻቸው ክሶች መካከል በፈረንጆቹ 2014 በዩክሬን የተመታው ኤምኤች17 የመንገደኞች አውሮፕላን በሩሲያ መመታቱን፣ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ላደረሰችው ጉዳት ካሳ ይከፈለኝ እና ሩሲያ ሽብርተኞችን ትደግፋለች የሚሉት ዋናዋና ክሶች ነበሩ።
ፍርድ ቤቱም ሩሲያ ለዩክሬን ካሳ ትክፈል የሚለው እና ኤምኤች17 አውሮፕላንን መታለች የሚለው ክስ ውድቅ ተደርጓል።
እንዲሁም ሩሲያ ሆን ብላ በክሪሚያ ያሉ ዩክሬናዊያንን ባህል እና ቋንቋ እያጠፋች ነው በሚል የቀረበው ክስ ውድቅ ቢደረግም ሞስኮ ለዩክሬናዊያን ቋንቋ መስፋፋት ትኩረት አለመስጠቷ ግን እንደ ጥፋት መታየቱን ሮይተርስ ዘግቧል።
ይህ የሁለቱ ሀገራት ክርክር የመጨረሻ ውሳኔ ያገኘ ሲሆን ይግባኝ ማለትም አይቻልም ተብሏል።