የፖሊዮ በሽታ በአፍሪካ ጠፋ ከተባለ ከአምስት አመት በኋላ በማላዊ መገኘቱን ድርጅቱ ገለጸ
የተገኘዉ ፖሊዮ (ዋይልድ ፖሊዮ) በፓኪስታን ውስጥ እየተዘዋወረ ካለው በሽታ የሚመሳሰል ነው ተብሏል
የፖሊዮ መድኃኒት ባይኖርም በክትባት መከላከል እንደሚቻል የዓለም ጤና ድርጅት መረጃዎች ያስረዳሉ
በማላዊዋ መዲና ሊሎንግዌ የፖሊዮ በሽታ እንደተከሰተ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ማወጃቸውን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።
የማላዊ ባለስልጠናት ፖሊዮ በሽታ መከሰቱን ያወጁት በአንድ ህጻን ልጅ ላይ ያደረጉትን ምርምራ ተከትሎ እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት የላብራቶሪ ትንታኔዎችን መሰረት በማድረግ ባወጣው መግለጫ እንዳመላከተው ከሆነ በማላዊ የተገኘዉ ፖሊዮ (ዋይልድ ፖሊዮ) በሽታው እየተሰራጨ ባለባት ባለው ፓኪስታን ውስጥ እየተዘዋወረ ካለው ስር የሰደደ በሽታ ጋር የተያያዘ ነው፡፡
ይሁን እንጅ በሽታው "ከፓኪስታን የመጣ እንደመሆኑ፡ ምርመራው ከፖሊዮ ቫይረስ ነፃ የማረጋገጫ ሰርተፊኬት ያገኘውን የአፍሪካን አካባቢ ሁኔታን የሚለውጥ አይደለም"ሲልም አክሏል።
ግሎባል ፖሊዮ ኢራዲኬሽን ኢኒሼቲቭ በበኩሉ በሽታው በደቡብ አፍሪካዊቷ ሀገረ ማላዊ የተከሰተው አሁን ሳይሆን ባለፈው ዓመት ህዳር ወር በአንዲት የሶስት ዓመት ልጅ ላይ ነበር ብለዋል፡፡
በወቅቱ የፖሊዮ ሰለባ ሆነቸው የሶስት ዓመት ልጅ ሽባ እስከመሆን የደረሰችበት አጋጣሚ እንደነበርም አስታውሷል ኢኒሼቲቩ፡፡
በደቡብ አፍሪካ ተላላፊ በሽታዎች ብሄራዊ ተቋም እና በአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማእከል በየካቲት ወር ባካሄዱት ምርምር የቫይረሱ ቅደም ተከተል ደብሊውፒ1 በመባል እንደሚታወቅ ማረጋገጣቸው ኢኒሼቲቩ አስታውቋል።
"ደብሊውፒ1 በፓኪስታን እና አፍጋኒስታን መገኘቱ ለፖሊዮ ክትባት ተግባራት ቅድሚያ የመስጠትን አስፈላጊነት አጉልቶ የሚያሳይ ነው"ም ብሏል ዓለም አቀፉ የፖሊዮ ኢራዲኬሽን ኢኒሼቲቭ እንደተናገረው።
የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ በአፍሪካ የሚከሰተውን በሽታ ለመግታት አፍሪካውያን ፈጣን ምላሽ መስጠት እንደሚችሉ ገልጿል።
በአለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቢሮ የፖሊዮ አስተባባሪ ሞጂሮም ንዱታቤ "በአፍሪካ የመጨረሻው የፖሊዮ ቫይረስ በሰሜን ናይጄሪያ በ2016 እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ 5 ግኝቶች ነበሩ፡፡ ማንኛውም የፖሊዮ ቫይረስ ጉዳይ ትልቅ ክስተት ነው እናም ሁሉንም ሀብቶች በማሰባሰብ የሀገሪቱን ምላሽ ለመደገፍ እንሰራለን" ሲሉ ተናግሯል፡፡
ፖሊዮ የነርቭ ሥርዓትን በመውረር በሰዓታት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ሽባ የሚያደርግ በጣም ተላላፊ በሽታ መሆኑ ይታወቃል፡፡
የፖሊዮ መድኃኒት ባይኖርም በክትባት መከላከል እንደሚቻል የዓለም ጤና ድርጅት መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡