በተያዘው ዓመት ከጥር ወር ጀምሮ ባሉት ሁለት ወራት ውስጥ ብቻ ከ19 ሺህ በላይ የኩፍኝ በሽታዎች ተከስተዋል ተብሏል
የኩፍኝ በሽታ በ79 በመቶ መጨመሩን የዓለም ጤና ድርጅት ገለጸ፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት እንዳስታወቀው የኩፍኝ በሽታ እንደ አዲስ ማገርሸቱን ገልጾ የኮሮና ቫይረስ እና ግጭቶች ለበሽታው መስፋፋት ዋነኛ ምክንያት መሆናቸውን ገልጿል፡፡
በፈረንጆቹ 2022 ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሁለት ወራት ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ በኩፍኝ በሽታ የተጠቁ ሰዎች ብዛት ከአምናው ተመሳሳይ ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ79 በመቶ መጨመሩን ድርጅቱ በድረገጹ አስታውቋል፡፡
በ2021 ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ በኩፍኝ በሽታ የተጠቁ ሰዎች ብዛት 9 ሺህ 665 የነበረ ሲሆን በተያዘው ዓመት ጥር እና የካቲት ውር ውስጥ 17 ሺህ 338 ሰዎች መጠቃታቸው ተገልጿል፡፡
ሶማሊያ፣ የመን አፍጋኒስታን፣ ናይጀሪያ እና ኢትዮጵያ በኩፍኝ በሽታ የተጠቁ ሀገራ ሲሆኑ ግጭቶች ፣ የሰዎች መፈናቀል እና የጤና መሰረተ ልማት በጦርነት መውደማቸው ለበሽታው መከሰት ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያ ባለፉት 12 ወራት ውስጥ 3 ሺህ 39 ሰዎች በኩፍኝ በሽታ የተጠቁ ሲሆን 58 በመቶዎቹ ደግሞ የመጀመሪያ ዙር ክትባት ማግኘታቸው ተገልጿል፡፡
በአብዛኛው ህጻናትን የሚያጠቃው የኩፍኝ በሽታ ተላላፊ በሽታ ሲሆን ተገቢው የሕክምና ክትትል ከተደረገ መዳን ይቻላል፡፡ ይሁንና በበሽታው ላለመጠቃት አስቀድሞ ክትባት መውሰድ ይመከራል፡፡
የኩፍኝ በሽታ ተገቢውን የህክምና ክትትል ካላገኘ ከመግደል ጀምሮ ዘላቂ ለሆነ የአዕምሮ ጉዳት፣ ለሳንባ ምች፣ ያለጊዜው ጽንስ መውለድ፣ ለመስማት ችግር እና ለሌሎች ጉዳቶች የሚዳርግ በሽታ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል፡፡
በፈረንጆቹ 2020፣ 20 ሚሊዮን ህጻናት የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት መውሰድ እያለባቸው ያልወሰዱ ሲሆን አሁን ለተከሰተው የኩፍኝ በሽታ የራሱ አስተዋጽኦ ማድረጉንም ድርጅቱ ገልጿል፡፡
ከሚያዝያ 1 ጀምሮ በ43 የዓለማችን ሀገራት ያሉ 203 ሚሊዮን ህጻናትን የበሽታ መከላከያ ክትባቶችን የመስጠት እቅድ ቢኖርም እስካሁን ክትባቱ አለመጀመሩ ተገልጿል፡፡
ክትባቱ ባለመሰጠቱ ምክንያትም 73 ሚሊዮን የዓለማችን ህጻናት የኩፍኝ ወረርሽኝ ሰለባ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያስጠነቀቀው የዓለም ጤና ድርጅት ሀገራት እና ዓለም አቀፍ የክትባት ኩባንያዎች ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡም አሳስቧል፡፡