የአውሮፓ ህብረት፤ ለሁሉም ተንቀሳቃሽ ስልኮች የሚሆኑ ወጥ ‘ቻርጀሮች’ እንዲመረቱ ሊያስገድድ ነው
‘ቻርጀሮች’ን ለመግዛት በየዓመቱ በግምት እስከ 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዩሮ ድረስ እንደሚወጣ ከህብረቱ የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ
ይህን ማድረጉ ቻርጀሮች ተነጥለው እንዳይሸጡ ከማድረግ ባለፈ የኤሌክትሮኒክ ብክነትን ለማስቀረት ያስችላል ተብሏል
የአውሮፓ ህብረት፤ ለሁሉም ተንቀሳቃሽ ስልኮች የሚሆኑ ወጥ ‘ቻርጀሮች’ እንዲመረቱ ሊያስገድድ ነው፡፡
ህብረቱ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ለሁሉም የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ አይነቶች የሚሆኑ ወጥ ቻርጀሮችን እንዲያመርቱ ሊያስገድድ እንደሚችል አስታውቋል፡፡
ኩባንያዎቹ ለዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስልኮች፣ ለታብሌት ኮምፒውተሮች፣ ለጆሮ ማዳመጫዎች እና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች የሚሆኑ ወጥ ዓለም አቀፍ ቻርጀሮችን እንዲያመርቱም ነው ህብረቱ የጠየቀው፡፡
“ኩባንያዎቹ በራሳቸው እንደሚያደርጉት ብንጠብቅም ያ ሊሆን ግን አልቻለም” ያሉት ምክትል የህብረቱ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ማርጋሬት ቬስታገር “እርምጃ የመውሰጃ ጊዜው አሁን ነው” ሲሉ ተናግረዋል ፡፡
እርምጃው ቀድሞውኑ በሰፊው ጥቅም ላይ የዋለው የ‘ዩኤስቢ-ሲ ፖርት’ ‘ቻርጀር’ በአውሮፓ ወጥ በሆነ ሁኔታ ግልጋሎት ላይ እንዲውል ማድረግን ታሳቢ ያደረገ ነው እንደ ዩሮ ኒውስ ዘገባ፡፡
ይህ ተቋማቱ ተጨማሪ ቻርጀሮችን እንዳይሸጡ ከማድረግም ባለፈ የኤሌክትሮኒክ ብክነትን ለማስቀረት እንደሚያስችል በህብረቱ ታምኖበታል፡፡
ከህብረቱ የተገኙ አሃዞች እንደሚያመለክቱት በዚህ መመሪያ ስር ማለፍ የነበረባቸው 420 ሚሊዮን ስልኮች እና የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች በባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ተሸጠዋል።
ሆኖም ለመሣሪያዎቹ የሚሆኑና ለብቻቸው የሚሸጡ ‘ቻርጀሮች’ን ለመግዛት በየዓመቱ በግምት እስከ 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዩሮ ድረስ ይጠፋል።
የውሳኔ ሃሳቡ ገና 27 አባል ሃገራት በተወከሉበት የህብረቱ ፓርላማ ቀርቦ አልጸደቀም፡፡
ኩባንያዎቹ ውሳኔው በአባል ሃገራቱ ፊርማ ከጸደቀ በኋላ እስከ ሁለት ዓመታት ድረስ ሁኔታውን ሊያጤኑ የሚችሉበት ጊዜ እንዳለ ህብረቱ አስታውቋል፡፡
ሆኖም ይህ የህብረቱ ሃሳብ አፕልን ጨምሮ ከተለያዩ ግዙፍ የዓለማችን የኤሌክትሮኒክስ አምራች ኩባንያዎች ከፍተኛ ተቃውሞ እየገጠመው ነው፡፡