በኮሮና ቫይረስ ምክኒያት የ2020 የአውሮፓ ዋንጫ ከአንድ ዓመት በኋላ በ2021 ይካሔዳል
በኮሮና ቫይረስ ምክኒያት የ2020 የአውሮፓ ዋንጫ ከአንድ ዓመት በኋላ በ2021 ይካሔዳል
በዚህ ዓመት ሊካሄድ የነበረው የአውሮፓ ዋንጫ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ወደ ሚቀጥለው ዓመት መዛወሩ ተገለጸ፡፡ ዜናውን ቀድሞ ያበሰረው የኖርዌይ እግር ኳስ ማህበር እንደገለጸው ውድድሩ እ.አ.አ በ2021 እንዲካሄድ ተወስኗል፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በቪዲዮ ኮንፈረንስ ባደረገው አስቸኳይ ውይይት ነው ውሳኔው የተላለፈው፡፡ ውሳኔው የአውሮፓ ሊጎች እንዲጠናቀቁ እድል ይሰጣል ተብሏል፡፡ የአውሮፓ ዋንጫ በአውሮፓውያኑ ከፊታችን ሰኔ 12 እስከ ሀምሌ 12 ሊካሄድ የነበረ ቢሆንም በ 2021 ከሰኔ 11 እስከ ሀምሌ 11 ይካሄዳል፡፡
የአውሮፓ ዋንጫ እንዲሁም ከ21 ዓመት በታች ውድድሩም ወደ ሚቀጥለው ዓመት የተሸጋገሩ ውድድሮች ናቸው፡፡
የአውሮፓ ዋንጫ የሴቶች ውድድር ደግሞ በሚቀጥለው ዓመት የወንዶቹ ውድድር ከተጠናቀቀ በኋላ እንደሚካሄድ መርሃ ግብር ወጥቶለታል፡፡
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በፈረንጆቹ እስከ ሚያዚያ አራት ድረስ የማይካሄድ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን የስፔን ላሊጋ በተመሳሳይ በፈረንጆቹ እስከ ሚያዚያ አራት ውድድሮቹ አይካሄዱም፡፡
በአውሮፓ ቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ የተበራከተባት ጣሊያንም ሊጓ ብቻ ሳይሆን ብዙ ክንውኖችም ተዘግተዋል፡፡በፈረንሳይም አሁን ላይ የሊግ አንድ ጨዋታዎች እየተካሄዱ አይደለም፡፡ የጀርመን ቡንደስሊጋ ደግሞ እስከ ሚያዚያ ሁለት 2020 ድረስ ውድድሮች አይኖሩትም፡፡
ምንጭ፡- ቢቢሲ