የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ክትባት ሙከራ በአሜሪካ ዛሬ ይጀመራል
የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ክትባት ሙከራ በአሜሪካ ዛሬ ይጀምራል
የአሜሪካ ባለስልጣናት እንዳስታወቁት በኮሮና ቫይረስ ክትባት ሙከራ ሂደት ውስጥ የመጀመሪያው ተሳታፊ የሚሞከረውን የክትባት መድሃኒት መጠን ዛሬ ይወስዳል፡፡
በሲያትል በሚገኘው በኬይሰር ፐርማነንቴ ዋሽንግተን የጤና ምርምር ኢንስትቲዩት የሚካሄደው የክትባት ሙከራ ከብሄራዊ የጤና ኢንስትቲዩት በተገኘ በጀት መሆኑን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
ሙከራው በግልጽ ይፋ ባለመደረጉ ምክንያት፣ የመጀመሪያው ታሳታፊ ላይ ክትባቱ እንደሚሞከር የገለጹት ባለስጣናት ስማቸውን ከመጥቀስ ተቆጥበዋል፡፡
ባለስልጣናቱ ለክትባቱ እውቅና ለመስጠት 18 ወራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የክትባቱ መኩራ የሚጀመረው ጤነኛና በጎ ፋቃደኛ በሆኑ 45 ወጣቶች ላይ ሲሆን፣ የክትባቱ መጠን እንደሚለያይም ተገልጿል፡፡
ክትባቱ ቫይረስ ስለማይኖረው፣ ተሳታፊዎች በሙከራው የሚጠቁበት እድል የለም ተብሏል፡፡ የሙከራው ዋና አላማ ክትባቱ ምንም የሚያስጨንቅ የጎንዮሽ ጉዳት አለመኖሩን ለማወቅና ሙከራው በሰፊው ለማካሄድ መሆኑ ተነግሯል፡፡
ከደርዘን በላይ የሚሆኑ የጥናት ቡድኖች የኮሮና ቫይረስን ክትባት ለማግኘት እየተሯሯጡ ባለበት ሰአት የበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል፡፡
ኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ
ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መጋቢት 4፣ 2012 በሰጡት መግለጫ በኮሮና ቫይረስ የተያዘ ሰው መኖሩን ይፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡
ግለሱቡ ጃፓናዊ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ የገባው የካቲት 25 መሆኑንና ከእሱ ጋር ንክኪ ያላቸው 25 ሰዎች ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑን ገልጾ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ እስካሁን በቫይረስ ተያዙ ሰዎች ቁጥር 5 ሲደርስ፣ በለይቶ ማቆያ ቦታ ደግሞ 117 ሰዎች የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡
ከቻይና ውሀን ግዛት የተነሳው የኮሮና ቫይረስ መላው ዓለምን አዳርሷል፡፡ ቫይረሱ እስካሁን ከ5,000 በላይ ለሆኑ ሰዎች ሞት ምክንያት ሲሆን 170,000 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ተይዘዋል፡፡