የፍልስጤም እግርኳስ ቡድን ለ2026ቱ የአለም ዋንጫ የመጨረሻ ዙር ማጣሪያ አለፈ
በጋዛ ባለው የጸጥታ ሁኔታ ምክንያት በዶሃ ጨዋታዎቹን የሚያደርገው የፍልስጤም ቡድን ትናንት ከሊባኖስ ብሄራዊ ቡድን ጋር ነጥብ ተጋርቷል
በታሪኳ በአለም ዋንጫ አንድ ጊዜ ብቻ የተሳተፈችው ቻይና ከታይላንድ ጋር አቻ መለያየቷ ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ እድሏን አጣብቂኝ ውስጥ ከቶታል
የፍልስጤም እግርኳስ ቡድን ለአለም ዋንጫ የመጨረሻ ዙር ማጣሪያ በማለፍ ታሪካዊ ውጤት አስመዘገበ።
በጋዛ ባለው የጸጥታ ሁኔታ ምክንያት በዶሃ ጨዋታዎቹን የሚያደርገው የፍልስጤም ቡድን ትናንት ከሊባኖስ ብሄራዊ ቡድን ጋር ነጥብ ተጋርቷል።
በምድብ ዘጠኝ ከአውስትራሊያ፣ ሊባኖስ እና ባንግላዲሽ ጋር የተደለደለው የፍልስጤም ቡድን ከሊባኖስ ጋር ትናንት በዶሃ ጃስሚን ቢን ሃማድ ስታዲየም ያደረገው ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎም አውስትራሊያ በ15:፥ ፍልስጤም ደግሞ በስምንት ነጥብ ወደ መጨረሻው ዙር ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።
ከፍልስጤም በአምስት ነጥብ ዝቅ ብላ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ያለችው ሊባኖስ የመጨረሻ ጨዋታዋን ብታሸንፍም ልዩነቱን ወደ ሁለት ዝቅ ከማድረግ ውጭ ትርጉም አይኖረውም።
በምድብ ሶስት ከደቡብ ኮሪያ፣ ታይላንድ እና ሲንጋፖር ጋር የተደለደለችው ቻይና በበኩሏ የ2026ቱ የአለም ዋንጫ የመጨረሻ ዙር ማጣሪያን የመቀላቀል ተስፋዋ አጣብቂኝ ውስጥ ወድቋል።
ትናንት ከታይላንድ ጋር 1 ለ 1 መለያየቷን ተከትሎ በ8 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ቻይና የፊታችን ማክሰኞ በ13 ነጥብ ምድቡን ከምትመራው ደቡብ ኮሪያ ጋር ትጫወታለች።
በሴኡል በሚደረገው ፍልሚያ ማሸነፍ ወይም ነጥብ መጋራት ቻይናን ለሶስተኛው ዙር ማጣሪያ እንድትደርስ ያደርጋታል።
ቻይና ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን በ2002 በጋራ ባዘጋጁት የአለም ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፋ ከምድቧ ምንም ጎል ሳታስቆጥርና ሁሉንም ጨዋታዎች ተሸንፋ መሰናበቷ ይታወሳል።
ጎረቤቷ ደቡብ ኮሪያ በበኩሏ ለ11ኛ ተከታታይ ጊዜ በአለም ዋንጫ ለመሳተፍ ተቃርባለች።
አረብ ኤምሬትስ፣ አውስትራሊያ፣ ኢራቅና ጃፓን በ15 ነጥብ አስቀድመው ወደ መጨረሻው ዙር ማለፋቸውን ያረጋገጡ ሲሆን፥ ሳኡዲ አረቢያም ፓኪስታንን 3 ለ 0 በማሸነፍ ምድቧን በ13 ነጥብ እየመራች አልፋለች።
ኳታር በ13 ነጥብ ከምትመራበት ምድብ 1 ህንድ እና አፍጋኒስታን ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ወደ መጨረሻው ዙር ማጣሪያ ለማለፍ ተፋጠዋል።
አሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ በጋራ በሚያዘጋጁት የ2016 የአለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች በተለያዩ ክፍላተ አለማት እየተካሄዱ ነው።