አሜሪካ የቪንዙዌላው ፕሬዝደንት ማዱሮ ያሉበትን ለጠቆማት 25 ሚሊዮን ዶላር እከፍላሁ አለች
የቬንዙዌላ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ለሶስተኛ ጊዜ በስልጣን መቆየት የሚያስችላቸውን ቃለ መሀላ ፈጽመዋል
ከአሜሪካ በተጨማሪ የአውሮፓ ህብረት እና ብሪታንያም ለፕሬዝዳንት ማዱሮ እውቅና እንደማይሰጡ አስታውቀዋል
አሜሪካ የቪንዙዌላ ባለስልጣናትን ለጠቆማት 40 ሚሊዮን ዶላር እከፍላሁ አለች፡፡
የተትረፈረፈ የነዳጅ ሀብት ካላቸው የዓለማችን ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ቬንዙዌላ ከምዕራባዊያን ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት ሻክሯል፡፡
የደቡብ አሜሪካዊቷ ሀገር ቬንዙዌላ ባሳለፍነው ሐምሌ ወር ላይ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ያደረገች ሲሆን ባለፉት 12 ዓመታት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሆነው ያገለገሉት ኒኮላስ ማዱሮ ምርጫውን እንዳሸነፉ አውጀዋል ተብሏል፡፡
ይህን ተከትሎም በትናንትናው ዕለት ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ለሶስተኛ ጊዜ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሆነው መቀጠል የሚያስችላቸውን ቃለ መሃላ ፈጽመዋል፡፡
በዓለ ሲመቱን ተከትሎም ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የቬንዙዌላ ባለስልጣናትን ለማሰር ጥቆማ ለሰጡ አካላት 40 ሚሊዮን ዶላር እንደሚከፍሉ መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን ለጠቆመ 25 ሚሊዮን ዩሮ እንዲሁም የሀገር ውስጥ ሚኒስትሩ ዲዎስዳዶ ካቤሎን ለጠቆመ ደግሞ 15 ሚሊዮን ዶላር እንደሚከፍሉም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ከአሜሪካ በተጨማሪም ብሪታንያ እና የአውሮፓ ህብረትም በቬንዙዌላ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ እና ካቢኔዎቻቸው ላይ ማዕቀብ ጥለዋል፡፡
ሀገራቱ በካራካስ ላይ እርምጃ የወሰዱት ዲሞክራሲን ጎድቷል፣ የሕግ የበላይነት እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ፈጽመዋል በሚል ነው፡፡
አሜሪካ እና ሌሎች ምዕራባዊን ሀገራት የተቃዋሚ ፓርቲው ኤድሙንዶ ጎንዛሌዝ የቬንዙዌላውን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫን እንዳሸነፉ እና የሀገሪቱ ህጋዊ ፕሬዝዳንት እንደሆኑ እውቅና ሰጥተዋል፡፡
ይሁንና ኤድሙንዶ ጎንዛሌዝ ከሀገር ተሰደው ወደ አሜሪካ የገቡ ሲሆን ፕሬዝዳንት ማዱሮ ጎንዛሌዝ ያለበትን ለጠቆመኝ 100 ሺህ ዶላር እከፍላሁ ብለዋል፡፡
የኩባ እና ኒው ካራጓ ፕሬዝዳንቶች በፕሬዝዳንት ማዱሮ በዓለ ሲመት ላይ የተገኙ መሪዎች ሲሆኑ ኢራን፣ ሩሲያ እና ቻይና ደግሞ የካራካስ ብቸኛ ወዳጅ ሀገራት ናቸው፡፡
ብራዚል እና ኮሎምቢያ ለፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ እውቅና እንደማይሰጡ ከተናገሩ የደቡብ አሜሪካ ሀገራት መካከል ናቸው፡፡