በዋሽንግተን በሚካሄደው የአሜሪካ-አፍሪካ ጉባኤ ላይ ያልተጋበዙ ሀገራት እነማን ናቸው?
በጉባኤው ላይ የሚገኙ እና ተወካይ የሚልኩ ሀገራትስ የትኞቹ ናቸው?
ኢትዮጵያስ በዚህ ጉባኤ ላይ ትሳተፋለች?
በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን መሪነት የተዘጋጀው የአሜሪካ እና አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ የፊታችን ማክሰኞ ጀምሮ ለሶስት ቀናት ይካሄዳል።
በአፍሪካ እና አሜሪካ ግንኙነት ላይ ትኩረቱን እንደሚያደርግ የሚጠበቀው ይህ ጉባኤ ከአምስት የአፍሪካ ሀገራት በስተቀር የ50 ሀገራት ፕሬዝዳንቶች እና ጠቅላይ ሚንስትሮች በዚህ ጉባኤ ላይ ይሳተፋሉ።
ፕሬዝዳንት ባይደን በዋሸንግተን በሚካሄደው በዚህ ጉባኤ ላይ የ49 ሀገራትን መሪዎች የጋበዙ ሲሆን 50 ተወካዮች እንደሚገኙ ቪኦኤ ዘግቧል።
እንደ ዘገባው ከሆነ አምስት የአፍሪካ ሀገራት በዚህ ጉባኤ ላይ ያልተጋበዙ ሲሆን ሱዳን፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ማሊ፣ ጊኒ እና ኤርትራ በጉባኤው ያልተጋበዙ ሀገራት ናቸው።
- ጆ ባይደን፤ የሩሲያ አፍሪካ ጉባዔ ከተካሄደ በኋላ የአፍሪካን መሪዎች ሊያገኙ ነው
- ጆ ባይደን፤ ከ110 ሃገራት መሪዎች ጋር ለማካሄድ ባሰቡት የበይነ መረብ ጉባዔ ጠ/ሚ ዐቢይን ሳያካትቱ ቀሩ
እነዚህ አምስት ሀገራት በጉባኤው ላይ ያልተጋበዙት በወታደራዊ አመራሮች ምክንያት በተፈጸመ መፈንቅለ መንግስት ምክንያት በአፍሪካ ህብረት በመታገዳቸው ነው ተብሏል።
በጉባኤው ላይ የተጋበዙት ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት የየሀገራቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይገኙ እንደሚችልም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
ደቡብ ሱዳን በዚህ ጉባኤ ላይ በውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ትወከላለች የተባለ ሲሆን ኢትዮጵያም በፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ትወከላለችም ተብሏል።
እንዲሁም የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ፣ የዚምባብዌው ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ምናጋግዋ እና ሌሎችም በጉባኤው ላይ እንደማይሳተፉ ተገልጿል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሙሳ ፋኪ ማሀማት፣ የናይጀሪያው ፕሬዝዳንት ሙሀመዱ ቡሀሪ፣ የአንጎላው ፕሬዝዳንት ፣የኬንያው ዊሊያም ሩቶ፣ የኡጋንዳው ዮሪ ሙሴቪኒ እና ሌሎችም ፕሬዝዳንቶች በጉባኤው ላይ ከሚሳተፉ የአፍሪካ መሪዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
በጉባኤው ላይ ስለ አፍሪካ ደህንነት፣ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ዲሞክራሲ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች የውይይቱ አካል እንደሚሆን ተገልጿል።