የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት አውሮፓ ጠንካራ አለመሆኗን እንዳሳየ ፊንላንድ ገለጸች
የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት የአውሮፓ ደህንነት በአሜሪካ ላይ እንዲመሰረት አድርጓል ተብሏል
አሜሪካ ባትኖር አውሮፓ አደጋ ውስጥ ሊወድቅ እንደሚችል ተገልጿል
የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት አውሮፓ ጠንካራ አለመሆኗን እንዳሳየ ፊንላንድ ገለጸች።
የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ወይም ኔቶን ለመቀላቀል በሂደት ላይ ያለችው ፊንላንድ የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት አውሮፓ ደካማ መሆኗን እንዳሳየ አስታውቃለች።
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳና ማሪን በአውስትራሊያ ሲድኒ ከተማ በተካሄድ የባለሙያዎች ውይይት መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር ጦርነቱ የአውሮፓን ድክመት አሳይቷል ብለዋል።
የዩክሬን ጦርነት የአውሮፓ ደህንነት በአሜሪካ ላይ ጥገኛ መሆኑን አሳይቷል በሚል የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሯ አውሮፓ የመከላከያ ደህንነቷን በራሷ ልታጠናክር ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
- ሩሲያ በዩክሬን ላደረሰችው ጉዳት 600 ቢሊዮን ዩሮ ካሳ መክፈል እንዳለባት የአውሮፓ ህብረት ገለጸ
- ዩክሬን ሩሲያን በአጭር ጊዜ ድል ማድረግ እንደማትችል የአሜሪካ ጦር ዋና አዛዥ ገለጹ
አውሮፓ በተለይም የጦር መሳሪያ ምርቶችን ጨምሮ በራሷ ማምረት እንዳለባት ያሳሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ማሪን አሜሪካ ባትኖር ኖሮ የአውሮፓ ደህንነት አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ አክለውም ስለ አውሮፓ ደህንነት ከአሜሪካ ፖለቲከኞች ጋር በተደጋጋሚ መምከራቸውን ተናግረው አውሮፓ አሁን ካለችበት የበለጠ መጠንከር እንዳለባት መስማማታቸውንም ጠቁመዋል።
አሜሪካ ለአውሮፓ ደህንነት ከፍተኛ መጠን ያለው የጦር መሳሪያዎች፣ የገንዘብ እርዳታ እና የሰብዓዊ ድጋፎችን ብትሰጥም አውሮፓ አሁንም አለመጠንከሯን ጠቅላይ ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ ከዚህ በፊት አውሮፓ በቻይና ቴክኖሎጂዎች ላይ ጥገኛ መሆኗን ገልጸው በተለይም በአርቲፊሺያል ኢንተለጀንስ፣ በኮምፒውተር ቴክኖሎጂ እና ሌሎችም የፈጠራ ስራዎች ዋነኞቹ እንደሆኑም አክለው ነበር።
አውሮፓ እና አሜሪካ የቻይናን ተገዳዳሪነት ለማስቀረት የ300 ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ቀርጸው ወደ ስራ መግባታቸውን ከዚህ በፊት በብሪታንያ በተካሄደው የቡድን ሰባት ሀገራት ጉባኤ ላይ መናገራቸው ይታወሳል።