በፈረንሳይ የታሰሩት ሰዎች ቁጥር 72 ሺህ 809 ደርሷል
በአውሮፓ የፍትህ አካላት በርካታ አስረኞችን በየወህኒ ቤቶች በማጎር የምትወቀሰው ፈረንሳይ በእስረኖች ቁጥር በአውሮፓ አዲስ ክብረ ወሰን አስመዘገበች፡፡
በቅርቡ በታተመው ኦፊሴላዊ አኃዛዊ መረጃ መሰረት በፈረንሳይ የታሰሩት ሰዎች ቁጥር 72 ሺህ 809 ደርሷል።
ይህ ማለት የአውሮፓ የሰብአዊ መብት ፍርድ ቤት በጥር 2020 ፈረንሳይን ባዘዘው መሰረት በእስር ቤቶች ውስጥ ያለውን መጨናነቅ የመቀነስ ተስፋ የለውም እንደማለት ነው፡፡
በፈረንሳይ የፍትህ ሚኒስቴር እንደፈረንጆቹ ህዳር 1 ባወጣው አኃዛዊ መረጃ እንደሚያመለክተውም 60 ሺህ 698 ሰዎች የመያዝ አቅም ባላቸው እስር ቤቶች 72 ሺህ 809 እስረኞች ይገኛሉ፡፡
የቀደመው ማለትም ከመጋቢት 2020 በፊት የነበረው የ72 ሺህ 575 እስረኞች ቁጥር የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመዋጋት የታቀደው እቅድን ተክተሎ በከፍተኛ ሁኔታ ቢቀንስም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ያለማቋረጥ ጨምሯል፡፡
ይህ አዝማሚያ የሚያሳየውም ባለፉት አስር አመታት የፈረንሳይ አጎራባች ሀገራት ውስጥ ከተመዘገበው ጋር ሲነጻጽር በፈረንሳይ ያለው የእስረኖች ቁጥር እያደገ መምጣቱ ነው፡፡
ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ የእስር መጠን በጀርመን በ12.9 በመቶ እንዲሁም በኔዘርላንድስ በ17 ነጥብ 4 በመቶ ሲቀንስ በፈረንሳይ የ4.3 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
በአንድ አመት ውስጥ በፈረንሳይ ውስጥ የእስረኞች ቁጥር በ 2 ሺህ 997 ጨምሯል እንደማለት ነው፡፡
በዚህም በእስር ቤቶች ባለው መጨናነቅ ምክንያት 2ሺህ 225 እስረኞች ወለል ላይ ፍራሽ አንጥፈው ለመተኛት መገደደቸው ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ዓለም አቀፉ የወህኒ ቤት ታዛቢዎች፣ የቦርዶ ጠበቆች ማህበር እና የታሳሪዎች መብት ተሟጋች ማህበር በፈረንሳይ ያለው የአስረኞች ሁኔታ እንደሚያሳስበው ገልጿል፡፡
ማህበሩ ይህንን "የእስረኞች መሰረታዊ መብቶችን የሚጥስ ከባድ እና አጠቃላይ ጥሰት" ለማስቆም ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ቢሞክሩም የፈረንሳይ ምክር ቤት የማህበሩ ጥያቄም ሆነ እርምጃ ውድቅ እንዳደረገበት ተሰምቷል።
የፈረንሳይ መንግስት በ2027 ተጨማሪ 15ሺህ አዳዲስ ወህኒ ቤቶችን በመገንባት የሚስተዋለውን ችግር ለምቅረፍ እንደሚሰራም ቃል ገብቷል ፡፡