በርካታ የአውሮፓ ሀገራት አስገዳጅ ብሄራዊ ውትድርናን ተግባራዊ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ ነው ተባለ
አሜሪካ ከአውሮፓ ጋር ያላትን ወታደራዊ ትብብር ለማቋረጥ ማሰቧን ተከትሎ አህጉሩ ራሱን ከጥቃት የሚከላከልበትን መንገድ እየቀየሰ ይገኛል

አብዛኞቹ የአውሮፓ ሀገራት ከቀዝቃዛው የአለም ጦርነት በኋላ ብሔራዊ ውትድርናን አስቀርተዋል
በርካታ የአውሮፓ ሀገራት ከአሜሪካ ድጋፍ ውጭ ራሳቸውን መከላከል የሚችሉበትን አቅም ለመፍጠር አስገዳጅ ብሔራዊ ውትድርናን ተግባራዊ ለማድረግ በስፋት እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡
የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ተስክ በቅርቡ ሁሉም በአዋቂ እድሜ ላይ የሚገኙ ወንዶች ወታደራዊ ስልጠና እንዲወስዱ የሚያስችል ረቂቅ እቅድ ለፓርላማው አቅርበው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ከፖላንድ ባለፈ ፈረንሳይ እና ጀርመን የሩስያ ወረራ ፍራቻን ወታደራዊ ወጪያቸውን ለማሳደግ እና አስገዳጅ ብሔራዊ ውትድርና ምልመላን ገቢራዊ ለማድረግ አቅደዋል፡፡
አሜሪካ ከአውሮፓ ጋር ያላትን የመከላከያ ግንኙነቷን ልታቋርጥ እንደምትችል መነገሩን ተከትሎ የዩክሬን ሁኔታ እንዳይደገም በመፍራት የአህጉሩ ሀገራት ማንኛውንም ጥቃት በመጋፈጥ የራሳቸውን አቅም ለማጠናከር የግዴታ ወታደራዊ አገልግሎትን እንደገና ለማስጀመር እያሰቡ ነው።
ነገር ግን ፈረንሳይን እና ብሪታንያን ጨምሮ ብዙ ሀገራት ወታደሮችን ለመመልመል እና ለማቆየት እየታገሉ ነው።
ወታደራዊ ተንታኞች በግዴታም ሆነ በፈቃደኝነት አንዳንድ የውትድርና አገልግሎትን ወደነበረበት መመለስ የበለጠ ከባድ ሊሆን እንደሚችል እየተናገሩ ነው፡፡
ዩጎቭ የተሰኘው የህዝብ አስተያየት የሚሰበስበው ተቋም ባሰባሰበው ድምጽ መሰረት 68 በመቶ ፈረንሳዊያን እና 58 በመቶ ጀርመናዊያን የወጣት ወንዶች የግዴታ ወታደራዊ ምልመላ አገልግሎት እንዲጀመር ይደግፋሉ።
በአንጻሩ ጣሊያኖች እና ብሪታኒያዎች በጉዳዩ ላይ ተከፋፍለዋል፤ 53 በመቶ የሚሆኑት ስፔናውያን በበኩላቸው አስገዳጅ ወታደራዊ ምልመላን ይቃወማሉ።
ብዙ አውሮፓውያን ሀገራቸውን በጦር ሜዳ ለመከላከል ዝግጁ እንዳልሆኑ ጥናቶች ያሳያሉ።
በህብረተሰቡ እና በወታደራዊ ሃይሎች መካከል ያለውን ትስስር የሚያጠናው ፈረንሳዊት ባለሙያ ቤኔዲክ ቺሮን “በሊበራል ማህበረሰብ ውስጥ ወታደራዊ ገደቦችን ማድረግ ፈጽሞ የማይቻል ነገር ነው” ይላሉ፡፡
ባለሙያዋ አክለውም “ወረራ እስካላጋጠመ ድረስ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ ዜጎችን የሚቀጣ መመሪያ ማውጣት ከፖለቲካ አንጻር ኪሳራን ሊስከትል እንደሚችል” ተናግረዋል፡፡
አብዛኞቹ የአውሮፓ ሀገራት ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላን የሰረዙ ሲሆን ፤ ግሪክ፣ ቆጵሮስ፣ ኦስትሪያ፣ ስዊዘርላንድ፣ ዴንማርክ፣ ኢስቶኒያ፣ ፊንላንድ፣ ኖርዌይ እና ቱርክ በበኩላቸው አሁንም ብሔራዊ ውትድርናን ገቢራዊ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል፡፡
የጀርመን አዲሱ ቻንስለር ፍሬድሪክ ሜርዝ ወታደራዊ ወይም የማህበረሰብ አገልግሎት ላይ ወጣቶች መሳተፍ እንዳለባቸው እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ብሪታንያ በበኩሏ የወታደራዊ ወጪን ማሳደግ እና የአውሮፓ ሀገራት ወታደራዊ ትብብር እንዲጠናከር እያስተባበሩ ይገኛሉ፡፡
በ2001 አስገዳጅ ብሔራዊ ውትድርናን ያስቀረችው ፈረንሳይ አገልግሎቱን ድጋሚ የምታስጅምርበትን መንገድ በመቃኘት ላይ ትገኛለች፡፡
የወታደራዊ ጥናት ባለሙያዎች አውሮፓ አሁን እየሰጋበት የሚገኘውን የሩስያን ጥቃት ለመከላከል አሁን በአህጉሩ ካሉ 1.47 ሚሊየን ወታደሮች ተጨማሪ 300 ሺህ ምልምሎች እንደሚያስፈልጉት ተናግረዋል፡፡