ሩሲያ በኩርስክ ያሉትን የመጨረሻዎቹን የዩክሬን ኃይሎች ለማስወጣት እየተዋጋሁ ነው አለች
ዩክሬን በኩርስክ ግዛት ድንገተኛ ጥቃት የከፈተችው የሩሲያን ኃይል ለማዛባትና ከሞስኮ ጋር ሊደረግ በሚችል የሰላም ንግግር እንደመደራደሪያ ለመጠቀም በማለም ነበር

የዩክሬን ወታደሮች የሩሲያን ድንበር በመጣስ ያደረሱት ጥቃት በ1941 የጀርመኑ ናዚ ከፈጸመው ጥቃት ወዲህ በሩሲያ ሉኣዊነት ላይ የተቃጣ ትልቅ ጥቃት ሆኖ ተመዝግቧል
ሩሲያ በምዕራብ ሩሲያ ኩርስክ ግዛት ከሰባት ወር በፊት ወረራ የፈጸሙትን የመጨረሻዎቹን የዩክሬን ኃይሎች ለማስወጣት ውጊያ እያደረገች እንደምትገኝ የሩሲያ ባለስልጣናት በትናንትናው እለት ተናግረዋል።
ዩክሬን ባለፈው ነሐሴ ወር በሩሲያ ኩርስክ ግዛት ድንገተኛ ጥቃት የከፈተችው በምስራቅ ዩክሬን ያለውን የሩሲያ ኃይል ለማዛባትና ከሞስኮ ጋር ሊደረግ በሚችል የሰላም ንግግር እንደመደራደሪያ ለመጠቀም በማለም ነበር።
የዩክሬን ወታደሮች የሩሲያን ድንበር በመጣስ ያደረሱት ጥቃት በ1941 የጀርመኑ ናዚ ከፈጸመው ጥቃት ወዲህ በሩሲያ ሉኣዊነት ላይ የተቃጣ ትልቅ ጥቃት ሆኖ ተመዝግቧል። ነገርግን የሩሲያ ኃይሎች በዚህ ወር በፈጸሙት መብረቃዊ ጥቃት በግዛቷ በዩክሬንን ቁጥጥር ስር የነበረውን የመሬት ስፋት ከ1368 ወደ 110 ስኩየር ኪሎሜትር ዝቅ አድርጎታል።
ተጽዕኖ ፈጣሪው የሩሲያ ደጋፊ የጦር ጸኃፊ ዩሪ ፖዶሊያካ ሩሲያ በተወሰኑ ቦታዎች የዩክሬን ወታደሮችን ወደ ድንበር ማስጠጋታቸውንና የዩክሬን ወታደሮች ወደ ኋላ በሚያፈገፍጉበት ወቅት ውጊያ መክፈታቸውን ጽፏል።
የሩሲያና የዩክሬን ጦር ሜዳ ካርታዎች የዩክሬን ኃይሎች በኩርስክ ግዛት በሩሲያ ድንበር በኩል ሁለት ቦታዎችን ይዘዋል። ሩሲያ በቦታው ብዙ ቁጥር ያለው ፈንጅ ማምከኗን ገልጻልች።
ፕሬዝደንት ትራምፕ በኩርስክ ግዛት ተከበዋል የተባሉ የዩክሬን ወታደሮች ህይወት እንዲተርፍ ጥሪ ካደረጉ በኋላ ፕሬዝደንት ፑቲን ወታደሮቹ እጅ የሚሰጡ ከሆነ ለህይወታቸው ዋስትና እንደሚሰጡ ተናግረው ነበር። የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ግን ወታደሮቹ አለመከበባቸውን ነገርግን ሩሲያ በሱሚ ግዛት አዲስ ጥቃት ልትከፍት እንደምትችል ተናግረዋል።
ፑቲንን በኩርስክ ግዛት በሚገኙ ንጹሃን ላይ ጉዳት በማድረስ የዩክሬን ወታደሮችን ከሰዋል፤ ነገርግን ኪቭ ክሱን አስተባብላለች።
ፕሬዝደንት ትራምፕ ሶስት አመታት ያስቆጠረውን ጦርነት ለማስቆም ከፕሬዝዳንት ፑቲንና ዘለንስኪ ጋር ወይይት እያደረጉ ይገኛሉ። ዘለንስኪ አሜሪካ ያቀረበችውን የ30 ቀናት ተኩስ ኡቀም የተቀበሉ ሲሆን ሩሲያ ማንኛውም ተኩስ አቁም ወደ ዘላቂ ሰላም የሚወስድ መሆን አለበት በማለት ቅደመ ሁኔታዎችን አስቀምጣለች። ሩሲያ የኔቶ ወደ ምስራቅ መስፋፋቱን እንዲያቆምና ዩክሬን የኔቶ አባል እንዳትሆን ትፈልጋለች።