“ዩኒቨርሲቲ አብሮኝ የተማረ ልጅ በ3 ሺህ ዶላር እንደሸጠኝ ያወኩት ቦታው ላይ ከታገትኩ በኋላ ነው”- ከምያንማር ወደ ሀገሩ የመጣ ኢትዮጵያዊ
ወደ ማያንማር የተጓዙ ኢትዮጵያዊን በሚያውቋቸው ኢትዮጵያዊያን ተታለው መጓዛቸውን ተናገግረዋል

በታይላንድ መንግስት እርዳታ ከእገታ የተለቀቁት ኢትዮጵያዊያን የመስራት አቅም የላቸውም ተብለው እንደሆኑ ተመላሾቹ ተናግረዋል
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእስያዊቷ ምያንማር የታገቱ፣ ለባርነት ተዳርገናል፣ ግፍ እየተፈጸመብን ነውና እርዱን የሚሉ ኢትዮጵያዊያንን ድምጽ እየተሰማ ነው፡፡
የሰለባዎቹ ኢትዮጵያዊያን ወላጆች፣ አንቂዎች እና መገናኛ ብዙሃንም ጉዳዩን ውሳኔ ወደሚሰጡ አካላት ለማድረስ የተለያዩ ጥረቶችን ማድረጋቸውን ተከትሎ ከቀናት በፊት በሁለት ዙር 77 ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡
ለራሳቸው እና ለቤተሰባቸው ደህንነት ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት ተመላሾች ወደ ምያንማር የሄዱት በሚያውቋቸው ሰዎች ተታለው እንደሆነ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
ከዩንቨርሲቲ ከተመረቀ በኋላ በቤተሰቦቹ እርዳታ በሐዋሳ ከተማ ንግድ ከፍቶ ሲንቀሳቀስ እንደነበር የገለጸ አንድ ተመላሽ እንዳለው ከሆነ አብሮት ዩንቨርሲቲ ይማር የነበረ የቀድሞ ጓደኛው አነሳስቶት ወደ ምያንማር ተጉዟል፡፡
“በጣም የማምነው ልጅ ነበር፣ በቴሌግራም አልፎ አልፎ እናወራ ነበር፡፡ የታይላንድ ዋና ከተማ በሆነችው ባንኮክ እንደሚኖር፣ በአንድ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ እንደሚሰራ እና በወር በትንሹ 120 ሺህ ብር ገቢ እያገኘ እንደሆነ ነገረኝ፡፡ እኔም ጓጉቼ እድል ካለ ፈልግልኝ አልኩት፡፡ እድሉ እንዳለ ከነገረኝ በኋላ ማሽኖቼን ሸጩ ወደ ባንኮክ አቀናሁ፡፡ ነገር ግን እዛ ስደርስ የተቀበለኝ ሌላ ሰው ነበር፡፡ የማላውቃቸው ሰዎች ኤርፖርት ውስጥ ተቀብለውኛል፣ አንተ የት ነህ ስለው አይዞህ እነሱ ናቸው አሰሪዎችህ ዝም ብለህ አርግ የሚሉህን አድርግ ተባበራቸው ምንም አትሆንም:: ወደ እኔ ነው እያመጡህ ያሉት ብሎኝ ማይንማር ግዛት ስንገባ በድንገት አድራሸውን አጠፋብኝ፣ ከዚያ በኋላ ለአራት ወራት ያለ ደመወዝ እና እረፍት አሰሩኝ” ሲልም አክሏል፡፡
ሌላኛው አስተያየት ሰጪም በተመሳሳይ በሚያውቀው ሰው መታለሉን የተናገረ ሲሆን አታለው ለሚያመጡ ለእያንዳንዳቸው ሰዎች ሶስት ሺህ ዶላር ድርጅቱ እንደሚከፍል እኔም በማንኛውም መንገድ አዲስ ሰው ካስመጣሁ ሶስት ሺህ ዶላር እንደሚከፈለኝ ቃል ተገብቶልኝ ነበር ብሏል፡፡
ለ10 ወራት በከባድ ስቃይ ውስጥ መቆየቱን የሚናገረው ይህ ተመላሽ ቤተሰቦቹ ሞቷል ብለው አምነው እንደነበር ነገር ግን በተዓምር ተርፎ ለሀገሩ መብቃቱን ጠቅሷል፡፡
ኢትዮጵያዊያኑን ጨምሮ በምይንማር እገታ ስር ያሉ ዜጎች ሁሉም በሚባል ደረጃ በባንኮክ በኩል የገቡ በመሆኑ የታይላንድ መንግስት ዓለም አቀፍ ጫና ሲበዛበት ባደረገው ጥረት የተወሰኑትን ሲያስለቅቅ እነሱም ለዚህ እድል መብቃታቸውን ተመላሾቹ ተናግረዋል፡፡
አል ዐይን ያናገረው ሶስተኛው ተመላሽ በቅርብ በሚያውቀው ሰው አማካኝነት የተሻለ ህይወት ፍለጋ ወደ ታይላንድ ከዚያ በማያውቃቸው ሰዎች አማካኝት ከሶስት ቀናት የመኪና ጉዞ በኋላ ማይንማር መግባቱን ተናግሯል፡፡
ወደ ታይላንድ ከመጓዙ በፊት ቤተሰቦቹ መኖሪያ ቤታቸውን አሲዘው በብድር ባወጡለት ገንዘብ ስራ ጀምሮ እንደነበርና ዕለታዊ ገቢ ያገኝበት የነበረውን ስራውን አቋርጦ ለህይወት ዘመን ችግር መዳረጉን አክሏል፡፡
በቀን ውስጥ 17 ሰዓት ያለ ዕረፍት የግዳጅ ስራ ሲሰራ እንደነበር የሚናገረው ይህ አስተያየት ሰጪ ተስፋ ቆርጬ ሞቴን እየተጠባበቅሁ እያለ በታይላንድ መንግስት እርዳታ እሱን ጨምሮ የተወሰኑ ኢትዮጵያዊን ከእገታ መለቀቃቸውን ነግሮናል፡፡
“ከማይንማር የተለቀቅነው መስራት አይችሉም፣ ገንዘብን አያስገኙልንም ብለው የለዩንን ነው፣ አጋቾቹ የመስራት አቅም አላቸው ብለው ያመኑባቸውን ይዘው አድራሻ ቀይረው ወደ ሌላ ቦታ ወስደዋቸዋል” ብሏል ይህ ተመላሽ፡፡
“ከደረሰብኝ የውስጥ ስባራት በተጨማሪ በስራ ጫና ምክንያት ለኩላሊት ህመም ተዳርጊያለሁ” የሚለው ይህ አስተያየት ሰጪ 350 ሺህ ብር መክሰሩንም ተናግሯል፡፡
አስተያየት ሰጪው አክሎም በእኔ ግምት አሁንም በማይንማር ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን በማይታወቅ ቦታ ለባርነት ተዳርገው አሉ ፣ መንግስትን ጨምሮ ሁሉም ጥረት
ኢትዮጵያዊያን በማይታወቅ ቦታ ለባርነት ተዳርገው አሉ ፣ መንግስትን ጨምሮ ሁሉም ጥረት እንዲደርግም ተመላሹ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የሌሎች ሀገራት ዜጎች ማያንማር ውስጥ ለሚገኙ የስካም(በኦንላይን አጭበርባሪ) ኩባያዎች ይሰሩ እንደነበር በርካታ አለምአቀፍ ሚዲያዎች ዘግበዋል።
ያነጋገርናቸው ተመላሾች "ስራ" የሚሉት የተሻለ ደሞዝ ታገኛለች በሚል ተታለው ከሄዱ በኋላ በስካም ኩባንያዎቹ ተገደው የሚፈጽሟቸውን ተግባራት ነው።
ኩባንያዎቹ ሰዎቹን በታይላንድ ድንበር በሚገኘው ካምፓቸው ካስገባቸው በኋላ ሀሰተኛ ማንነት እንዲላበሱ በማድረግ የሌሎች ሀገራት ዜጎችን ገንዘብ ከማጭበር እስከ ክሪፕቶ ማጭርበርና ህገወጥ ቁማር ድረስ ያሉ የወንጀል ተግባራትን እንዲፈጽሙ እንደሚያስገድዷቸው ሲገለጽ ቆይቷል።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተደጋጋሚ በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ በህገወጥ ሰዎች አዘዋዋሪዎች ተታለው ወደ ታይላንድ እና ማይንማር የተጓዙ እና ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን ለመርዳት እየተንቀሳቀስ መሆኑን መናገሩ ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያዊያኑ ለዚህ ጉዳት የተዳረጉት በምናውቃቸው እና በኢትዮጵያዊያን ነው ማለታቸውን ተከትሎ ተጎጂዎችን ወደ ሀገራቸው ከመመለስ ባለፈ አዘዋዋሪዎችን ተጠያቂ ለማድረግ የተጀመረ ጥረት እያደረገ እንደሆነ ላቀረብነው ጥያቄ ሚኒስቴሩ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡
ሚኒስቴሩ በሁለት ዙር 77 ኢትዮጵያዊያንን ከምይንማር ወደ ሀገራቸው በያዝነው ሳምንት መመለሱን ገልጿል፡፡
ተጨማሪ ኢትዮጵያዊያንን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ታይላንድ እና ጃፓን ባሉ የኢትዮጵያ ኢምባሲዎች በኩል ጥረቱ እንደሚቀጥልም ከዚህ በፊት በሰጠው መግለጫ ላይ ጠቅሷል፡፡