አሜሪካ በየመን የሀውቲ ይዞታዎች ላይ መጠነሰፊ ጥቃት ፈጸመች
ትራምፕ ቡድኑ በቀይ ባህር የመርከቦች እንቅስቃሴ ላይ እያደረሰ ያለውን ጥቃት ለጥቃቱ መፈጸም ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል

ለሀማስ አጋርነት ለማሳየት በቀይ ባህር በሚንቀሳቀሱ መርከቦች ላይ ጥቃት ማድረስ የመጀረው ቡድኑ ለአየር ጥቃቱ የአጸፋ ምላሽ እሰጣለሁ ብሏል
አሜሪካ በየመን የሀውቲ ይዞታዎች ላይ መጠነሰፊ ጥቃት ፈጸመች።
ፕሬዝደንት ትራምፕ አሜሪካ በየመን የሀውቲ አማጺያን ይዞታ ላይ"ወሳኝ እና ከባድ" የአየር ጥቃት መፈጸሟን ተናገሩ።
ትራምፕ ቡድኑ በቀይ ባህር የመርከቦች እንቅስቃሴ ላይ እያደረሰ ያለውን ጥቃት ለጥቃቱ መፈጸም ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።
"በኢራን የሚደገፉት የሀውቲ ታጣቂዎች ወደ የጦር ጄቶቻችንና ወታደሮችን እንዲሁም ወደ አጋሮቻችን ተኩሰዋል" ያሉት ትራምፕ "ዝርፊያቸው፣ጥቃታቸው እና ሽብራቸው" በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ማክሰሩንና ህይወትን አደጋ ላይ መጣሉን አክለው ተናግረዋል።
የሀውቲ የጤና ሚነስቴር እንደገለጸው በአየር ጥቃቱ 15 ሰዎች መገደላቸውንና ሌሎች ዘጠኝ ሰዎች መቁሰላቸውን ገልጿል። ነገርግን በጥቃቱ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር 31 መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
ከእስራኤል ጋር እየተዋጋ ላለው ለፍልስጤሙ ሀማስ ጋርነት ለማሳየት በቀይ ባህር በሚንቀሳቀሱ መርከቦች ላይ ጥቃት ማድረስ የመጀረው ቡድኑ ለአየር ጥቃቱ የአጸፋ ምላሽ እሰጣለሁ ብሏል።
ቅዳሜ ምሽት ሀውቲዎች በሰንዓና በሳኡዲ አረቢያ ድንበር በሚገኘው ዋና ይዞታቸው በሆነው ሰአዳ ግዛትና በሰንዓ ተከታታይ ፍንዳታዎች መከሰታቸውን ሪፖርት አድርገዋል። እስራኤልን ጠላት አድርጎ የሚያየውና በኢራን የሚደገፈው አማጺ ቡድኑ ሰንዓንና አብዛኛውን ሰሜን ምዕራብ የመን የተቆጣጠረ ቢሆንም በአለም አቀፍ ደረጃ የመንግስት እውቅና አላገኘም።
ሀውቲዎች ባወጡት መግለጫ አሜሪካንና ዩናይትድ ኪንግደምን(ዩኬን) በሰንዓ በሚገኙ የመኖሪያ መንደሮችን ኢላማ አድርገዋል ሲል ከሷል።
ፕሬዝደንት ትራምፕ "አንታገስም" ብለዋል። ትራምፕ አክለውም "አላማችንን እስከምናሳካ ድረስ ከባድ ጥቃት እንሰነዝራለን" ብለዋል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አርጋች አሜሪካ ኢራን በምትከተለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ አቅጣጫ ማሳየት የለበትም ብለዋል።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አሜሪካ "የእስራኤልን ዘር ማጥፋትና ሽብርን መደገፏን ታቁም"፤ "በየመን የምትፈጽመውን ግድያ ታቁም" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።
ለሀማስ አጋርነት ለማሳየት ከህዳር 2023 ጀምሮ ጥቃት እየፈጸሙ መሆናቸውን የገለጹት ሀውቲዎች እያጠቁ ያሉት ከእስራኤል፣ ዩኬና አሜሪካ ጋር ግንኙነት ያላቸውን መርከቦች ብቻ እንደሆኑ ይገልጻሉ።