የበሽር አላሳድ መንግስት መውደቅን ተከትሎ የጥገኝነት ጥያቄ መቀበል ያቋረጡ ሀገራት
በሶሪያ ጦርነት ከ6.3 ሚሊየን በላይ ዜጎች ሀገራቸውን ለቀው ተሰደዋል
እስከ ህዳር 2024 ድረስ በአጠቃላይ ከ14 ሚሊየን በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል
የሶሪያ አማጽያን ዋና ከተማዋ ደማስቆን ከተቆጣጠሩ እና የፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድ መንግስት ከስልጣን መወገድን ተከትሎ የአውሮፓ ሀገራት በሶሪያውያን እየቀረበላቸው የሚገኘውን የጥገኝነት ጥያቄ መቀበል ማቆማቸውን አስታውቀዋል፡፡
ሀገራቱ ከሶሪያ የሚመጡ የስደተኛ ሰነዶችን በሀገሪቱ ውስጥ በሚገኘው ያልተረጋጋ ሁኔታ ምክንያት መመልከት ማቆማቸውን ነው የገለጹት፡፡
በ2011 የተቀሰቀሰው የአረብ ጸደይ መንግስታዊ ቁመናቸውን ከነቀነቀባቸው ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ሶሪያ በዘመናዊው የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ የሰብአዊ ቀውስ ካስከተሉ ጦርነቶች መካከል አንዱ ታካሂዶባታል፡፡
ከ50 አመታት በላይ የዘለቀውን የአሳድ ቤተሰብ አገዛዝ ለመጣል በተለያዩ ታጣቂ ሀይሎች ለ13 አመታት ሲደረግ በነበረው ጦርነት 6.3 ሚሊየን ዜጎች ከሀገራቸው ተሰደዋል፤ አልያም የጥገኝነት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
ከዚህ ውስጥ 1.3 ሚሊየን የሚሆኑት በአውሮፓ ውስጥ ጥገኝነት ያገኙ ሲሆን 7.2 ሚሊየን የሚሆኑት ደግሞ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ናቸው፡፡
እንደ ተመድ የስደተኞች ድርጅት መረጃ ከሆነ እስከ ህዳር 2024 ድረስ በአጠቃላይ 14 ሚሊየን የሚጠጉ ሶሪያውያን በሀገር ውስጥ እና በውጭ ተፈናቅለው ይገኛሉ፡፡
ጥብቅ የስደተኞች አቀባበል ፖሊሲ ያላት ዴንማርክ ከ2015 ጀምሮ ሶሪያውያን በፈቃደኝነት እንዲመለሱ በማበረታታት ከዘላቂ ይልቅ ጊዜያዊ የመኖሪያ ፍቃድ መስጠት ላይ አተኩራ ቆይታለች፡፡
በዚህ አመት 1933 ሶሪያውን ጥገኝነት ጠያቂዎችን የተቀበለችው ኖርዌይ ስደተኞችን መቀበል ያቆመች ሌላኛዋ ሀገር ስትሆን፤ የስደተኞች አገልግሎት በአሁኑ ጊዜ በኖርዌይ ሶሪያውያን ያቀረቡትን የጥገኝነት ጥያቄ አይቀበልም ወይም አያፀድቅም ስትል አስታውቃለች፡፡
ጣሊያን ፣ ብሪታንያ ፣ ቤልጂየም ፣ ስዊድን ፣ ኦስትርያ ፣ እና ጀርመን አዲስ ውሳኔ ላይ እስከሚደርሱ ድረስ በጊዜያዊነት ስደተኞችን መቀበል ያቆሙ ሀገራት ናቸው፡፡
ከ2011 ጀምሮ በመካከለኛው ምስራቅ የተቀሰቀሰውን ቀውስ ተከትሎ ሶሪያውን ስደተኞችን በመቀበል ቱርክ ቀዳሚዋ ስትሆን 3.5 ሚሊየን ሰዎችን ይዛለች፤ ሊባኖስ ፣ ዮርዳኖስ ፣ ጀርመን ፣ ኢራቅ እና ግብጽ በተከታታይ በደረጃ ይገኛሉ፡፡